#Ethiopia‘s renowned environmental scientist and researcher, Dr. Tewolde Berhan Gebre Egziabher, has passed away today at the age 0f 83, families and friends announced.
Dr. Tewolde, who was the former Director General of Ethiopia’s Environmental Protection Authority, leaves behind a towering legacy of his invaluable researches on biodiversity, community (farmers’ rights) and his emphatic fight against unregulated genetically engineered crops.
Winner of, among their awards, the “Alternative Nobel Prize” and “Hero of our Earth”, Dr. Twewolde is survived by his three daughters.
Via Addis Standard

ዶ/ር ተወልደን በጨረፍታ
—–
በዘመነ ኢህአዴግ ከነበሩት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት መካከል በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታና ተወዳጅነት የነበራቸው በፎቶው ላይ የምትመለከቷቸው ዶ/ር ተወልደ-ብርሃን ገብረእግዚአብሄር ናቸው፡፡ ዶ/ር ተወልደብርሃን በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ላደረጉት ምርምርና በጉዳዩ ዙሪያ ከፍተኛ ግንዛቤ እንዲፈጠር ላደረጉት ጥረት በፈረንጆቹ 2000 ዓመት ዓለም አቀፉን የአቋራጭ ኖቤል ሽልማት (በትክክለኛ ስሙ Right Livlihood Award የሚባለውን) ተሸልመዋል፤ ይህንን ፎቶ የተነሱትም ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ነው፡፡ ዶ/ር ተወልደ በፈረንጆቹ 2006 ዓመትም የተባበሩት መንግሥታት በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች የሚሸልመውን Champions of the Earth ሽልማት አግኝተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በ1997 የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቶአቸዋል፡፡
እኚህ ሰው የሀገራችንን የብዝሀ-ህይወት ኢኒስቲትዩት ከማቋቋማቸውም በላይ ዝርያቸው ለመጥፋት የተቃረበ ሀገር በቀል ዛፎችን በሰፊው በማጥናት ለዘራቸው ጥበቃ የሚደረግበት የኢትዮጵያ ጄኔቲክ ባንክ እንዲመሰረት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የሀገራችንን የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ የቀየሱትም እርሳቸው ናቸው፡፡ በተጨማሪም ዶ/ር ተወልደ የአፍሪቃ ሀገራት የአሜሪካና የአውሮጳ ኩባኒያዎች ወደ ከባቢ አየር በሚለቋቸው በካይ ጋሶች ለሚደርስባቸው ጉዳት ተመጣጣኝ የካሳ ክፍያ እንዲጠይቁ ካስተባበሩት መሪዎች አንዱ ናቸው፡፡
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሄር በትግራይ ክልል በአድዋ ከተማ አቅራቢያ ባለችው “አዲ-እስላም” የተሰኘች የገጠር መንደር ነው የተወለዱት፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1955 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተቀበሉ በኋላ የማስትሬትና ዶክትሬት ዲግሬአቸውን ከዌልስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ዶ/ር ተወልደ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ1975 እስከ 1983 በነበረው ዘመን ደግሞ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ሰርተዋል፡፡ አስመራ በህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ስትከበብ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በያኔው የደርግ ካቢኔ ውስጥ የባህል ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነው አገለገሉ፡፡ የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላም ለብዙ ዓመታት በሚታወቁበት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡
ይህንን ካልን ዘንዳ ዶ/ሩ የባለስልጣኑ ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት ይቀርብባቸው የነበረውን አንድ ቅሬታ መጠቆም እንፈልጋለን፡፡ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ከአውሮጳ የመጡ የአበባ አምራችና ላኪ ኩባኒያዎች ሀገራችንን አጥለቅልቀዋታል፡፡ እነዚህ አምራቾች አበባውን ወደ ውጪ ልከው የውጪ ምንዛሬ ማምጣታቸው ጥሩ ነገር ቢሆንም አበቦችን በማምረት ሂደቱ የሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎች ከፍተኛ የአካባቢ ብክለትን የሚያስከትሉ መሆናቸው በልዩ ልዩ ምሁራን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች በመሬት ውስጥ የሚኖሩ ጠቃሚ ነፍሳትን (micro organisms) ይገድላሉ ይባላል፡፡ የውሃ ዑደትንም እንደሚያዛቡ ይነገራል፡፡ በትነት መልክ እየቦነኑ አየሩን እንደሚበክሉም በሰፊው ሲጻፍ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በአበቦቹ ማሳ ዙሪያ የሚኖረው አራሽ ማህበረሰብ ጤናማ የምግብ ስርዓት እንደማይኖረው ተገልጿል (አንዳንዶቹ ኩባኒያዎች በአካባቢ ላይ ሲያደርሱት በነበረው ጉዳት ምክንያት ከኬኒያና ከኡጋንዳ ተባረው መምጣታቸው በሰፊው ሲጻፍ የቆየ ጉዳይ ነው)፡፡
ታዲያ “ዶ/ር ተወልደ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተር ሆነው በሚሰሩበት ወቅት እነዚህ ሀገር አጥፊ ኩባኒያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እንዴት ፈቀዱ? ” የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች “ዶ/ር ተወልደ በሌሎች መድረኮች ላይ ሲያሰሙት የነበረውን ድምጽ በነዚህ ኩባኒያዎችም ላይ ማሰማት ነበረባቸው” ባይ ናቸው፡፡ ይሁንና ዶ/ር ተወልደ በአንድ ወቅት በጉዳዩ ዙሪያ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነገሩን በቸልታ እንዳላለፉትና ኩባኒያዎቹን መቆጣጠሩ ከአቅማቸው በላይ በላይ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ እርሳቸውን ከሾመው መንግሥት ጋር ልዩነት እንዳላቸውም አስታውቀዋል፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የኬሚካሎቹን አጥፊነትና ከመናገር እንዳልተቆጠቡም ተናግረዋል፡፡
——
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረእግዚአብሄር የታዋቂው ደራሲ የስብሐት ገብረእግዚአብሄር ታናሽ ወንድም ሲሆኑ ባለቤታቸው እንግሊዛዊቷ ሚስስ ሱ ኤድዋርድስ ናት፡፡ ገጣሚ ሮማን ተወልደ ደግሞ የመጀመሪያ ልጃቸው ናት።
ጋሼ ስብሐት “ማስታወሻ” የሚል ርዕስ ባለው የዘነበ ወላ መፅሐፍ “ከተወልደ የሰማሁት ማስተር ፒስ ተረት ነው” ብሎ የገለጸውን እንጋብዛችሁና እናብቃ፡፡
በአንዲት የገጠር መንደር ነው፡፡ አንድ ሰውዬ ከሩቅ ቦታ የመጣ የለቅሶ ድምጽ ይሰማል፡፡ ከዚያው ገደማ የመጣ ገበሬ ያይና “አንተዬ! ያቺ ሴትዮ ምን ሆና ነው የምታለቅሰው” በማለት ጠየቀው፡፡ ገበሬውም “እባክህ ተዋት! እርሷ ልጇ ሞታ ነው የምታለቅሰው፤ እኔ አለሁ አይደለም እንዴ ማረሻዬ ጠፍቶብኝ በፍለጋ የምንከራተተው?” በማለት ያልጠበቀውን መልስ ሰጠው፡፡
——
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 12/2007 ተጻፈ።