ወለጋ- የውቦች ምድር

ዛሬ በኢትኖግራፊ ፈረሳችን ገስግሰን ላለፉት አራት ዓመታት መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተውን የወለጋን ምድር ልንዘይረው ተዘጋጅተናል፡፡ ጉዞ ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ! ዳይ! ዳይ! ዳይ!’

የወለጋ ምድር የእናት ጓዳ ማለት ነው፡፡ ከዚያ ምድር የሚፈልቁት የኦሮሞ ባህላዊ ምግቦች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ጩምቦ፣ አንጮቴ፣ ጨጨብሳ፣ ጩኮ፣ መርቃ (ገንፎ) ሁላቸውም ጣት ያስቆረጥማሉ፡፡ የወለጋ ሴትን ያገባ እንዴት የታደለ መሰላችሁ? እጅግ ሲበዛ ሙያተኞች ናቸው፡፡

ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር በገጣሚ ሰለሞን ዼሬሳ ተጋብዞ ነቀምቴ በሄደበት ጊዜ ባየው የወለጋ ባህላዊ ቡፌ ተመስጦ ፍዝዝ ብሎ መቅረቱን ነግሮን ነበረ፡፡ በ2009 ያረፈው ታዋቂ ፖለቲከኛና ጠበቃ ጋሽ አሰፋ ጫቦ በበኩሉ የደርግ ዋነኛ ሰው ከነበሩት ኮሎኔል ደበላ ዺንሳ ጋር ወደ ወለጋ ሄዶ ያጋጠመውን ግብዣ ሲጽፍ “ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል” ነበር ያለው፡፡

እኔም በልጅነቴ “ጩምቦ-ጉልበተኛው ምግብ” የሚል ጽሑፍ ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ባነበብኩ ጊዜ በጣም ነበር የተገረምኩት፡፡ ጸሐፊው “በአንዲት አነስተኛ ሳህን የቀረበልንን ምግብ ስምንት ሆነን መጨረስ አቅቶን ነበር” ያለ ይመስለኛል (የምግቡ ዋነኛ ማሰናጃ “ቅቤ” ስለሆነ ነው ብዙ ሆነው ሊጨርሱ ያልቻሉት)፡፡ እዚህ ላይ “መሮሌ” ከተሰኘው የዘሪሁን ወዳጆ ዘፈን የተወሰኑ ስንኞችን ቀንጨብ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ዘሪሁን እንዲህ ነበር ያለው፡፡

As koottu Arjoo dhaqnee buna qalaa qalannaa

As koottu Qeellam deemnee marqaa garbuu kutannaa

ኦሮምኛውን ወደ አማርኛ ስንመልሰው እንዲህ ሊሆን ይችላል፡፡

ወደዚህ ነይ አርጆ ሄደን “ቡና ቀላን” እንቀምሳለን

ወደዚህ ነይ ቄለም ደርሰን የገብስ ገንፎ እንጎርሳለን፡፡

“ቡና ቀላ” ከቅቤ ጋር የሚቀቀል ቡና ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ቡናው በቅቤ ውስጥ ተነክሮ በምጣድ ላይ ይጠበሳል፡፡ በኦሮሞ ባህል መሠረት “ቡነ-ቀላ” የሚጋበዘው የክብር እንግዳ ወይንም የነፍስን ያህል የሚሳሱለት የቅርብ ወዳጅ ብቻ ነው፡፡ የወለጋ ሴቶች “ቡነ-ቀላ”ን ባማረ መዓዛ በማዘጋጀት ይታወቃሉ፡፡

*****

ጓዶች! የወለጋ ሴቶች በሙያቸው ብቻ አይደለም የሚታወቁት፡፡ በውበታቸውም የዘወትር ተጠቃሽ ናቸው፡፡ “ውቢት ኢትዮጵያ”ን የሚረሳ አለ? አዎን! ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን “የአስራ ሶስት ወር ፀጋ” በሚል ርእስ በሚያሳትማቸው ዝነኛ ፖስት ካርዶች ላይ የምናውቃት “ውቢት ኢትዮጵያ” የተሰኘችው ወጣት የወለጋ ልጅ ናት (ሙሉ ስሟ “ውቢት አመንሲሳ” ነው)፡፡

በልጅነቴ የማውቃት አንዲት ከወለጋ የመጣች ውብ ሴት ደግሞ በገለምሶ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታስተምር ነበር፡፡ ያቺ ወጣት በዚያ ዘመን በገለምሶ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት ከነበሩት ሁለት ሴት መምህራን አንዷ ነበረች፡፡ የወጣቷ ስም “ደሜ ኩምሳ” ነው፡፡ “ደሜ” በእርግጥም የተዋበች ሴት ነበረች (ደርግ ሊወድቅ በሚንገዳገድበት ሰሞን ደግሞ ደሜ ኩምሳ የታዋቂዋ የኦሮሞ መብት ታጋይ የዶክተር ኩዌ ኩምሳ እህት መሆኗን ተረድቻለሁ፡፡ ደሜ አሁን የአሜሪካ ነዋሪ ናት)፡፡

ይግረምህ እንግዲህ! ፈጣሪ ብሎልህ ከወለጋ ኮረዳዎች መካከል አንዷ ካንተ ጋር ከተጣመረች ከንፈር ለከንፈር እየተሞጫሞጫችሁ ማለቃችሁን እወቅ፡፡ ታዲያ ወለጊቷን ዝም ብለህ የምትስማት እንዳይመስልህ፡፡ የወለጋዋ ኮረዳ ፍቅሯ የሚጣፍጥላት “ሰው ሰው” በሚሸት ትንፋሽ ስትቀርባት ነው፡፡ የምልህ ገብቶሃል አይደለም? “ሰው ሰው” የሚሸት ትንፋሽ የሚለውን አስምርበት! “ቢኖ ቢኖ” እየሸተትክ እንዳትወሸክት! ከጎረና ትንፋሽ በጊዜ ራስህን ማፅዳት አለብህ፡፡

ለዚህ ፍቱን መድኃኒቱ ደግሞ “ኮረሪማ ማኘክ” እንደሆነ ገጣሚ ሰለሞን ዼሬሳ ነግሮናል፡፡ “ሰለሞን ዼሬሳ ወልለቱ ዘኢትዮጵያ ዘብሄረ ኦሮሞ ወ-ዘምድረ ወለጋ”ን ታውቁት የለምን?! ነፍሱን ይማረውና በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ል. ያረፈው ጎምቱ ባለቅኔ ማለታችን ነው፡፡ ያ “ልጅነት”ን እና “ዘበት እልፊቱ”ን የደረሰው ቱባ ገጣሚ!

ሰለሞን የተወለደው “ጨታ” በተባለች የወለጋ መንደር ነው፡፡ በዚያች መንደሩ እስከ ጉርምስናው ድረስ ኖሯል፡፡ ታዲያ ሰለሞን “ዘበት እልፊቱ” በተሰኘችው የወለሎ መጽሐፉ እንዳጫወተን ከሆነ የወለጋ ሸበላዎች ኮረሪማ ማኘክ የሚጀምሩት የጉርምስና ምልክት ሲመጣባቸው ነው፡፡ ሸበላው የራሱን ተጣማሪ እስኪያገኝ ድረስ ኮረሪማውን እያኘከ እና ትንፋሹን እያሳመረ በተስፋ ይቆያል፡፡ መለሎዋን ሲያገኝ ደግሞ መሳሳም ይጀምራል፡፡

ታዲያ የወለጋው ሸበላ ኮረዳዋን የሚስመው እንዲሁ ከመንገድ ላፍ አድርጎአት አይደለም፡፡ ጉብሊቷ ለእንጨት ሰበራ እና ውሃ ለመቅዳት ወደ መስክ ስትወጣ ይመጣና ውበቷን እያደነቀ ይዘፋፍንላታል፡፡ ከዚያም በራሱ ላይ እንደ ሻሽ አድርጎ የጠመጠመውን ነጠላ በማውረድ ከልጅቷ ጋር ይከናነበዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሁለቱ ወጣቶቹ የሚሳሳሙት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶቹ ለኢያሴ እና ለሌሎች ጨዋታዎች ተቀጣጥረው በሚገናኙበት ወቅት በጨዋታው መሃል የአፍታ እረፍት ወስደው ሊሳሳሙ ይችላሉ፡፡

ጥብቅ ማሳሰቢያ! የወለጋው ደርገጌሳ (ሸበላ) ፍቅረኛውን ከመሳም ባለፈ ለሌላ ነገር አይጋብዛትም፡፡ በየትኛውም የኦሮሚያ ዞን ባሉት ገጠሮች ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ወጣቶች ፍቅራቸውን የሚገልጹበት የመጨረሻው ድርጊት መሳሳምና መተቃቀፍ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ለወሲብ መገባበዝ በባህላቸው ውስጥ የለም፡፡ በኦሮሞ ባህል ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸም በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

—–

ወለጋ የጥበብ ምድር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከደምቢ ዶሎ ከተማ ብቻ የፈለቁትን የጥበብ ዋርካዎች ብቆጥርላችሁ ትገረማላችሁ፡፡ ሰለሞን ደነቀን ታውቁት የለም?… አዎን! ውብ በሆኑ የኦሮምኛ እና የአማርኛ ዜማዎቹ የምናውቀው ያ ወጣት የደምቢ ዶሎ ቡቃያ ነበር፡፡ ብዙዎቻችን ሰለሞንን የምናስታውሰው በ1980 በለቀቀው የመጀመሪያ አልበሙ ነው፡፡ በዚያ አልበም የተካተተው የኦሮምኛ ዜማ የሚከተለው አዝማች ነበረው፡፡

ያ ደበሌ ዝማሙ ያ ደበሌ ዝማሙ ( አንቺ ደበሌ ዝማሙ ሆይ)

አመልሊ ኬ ጉዳዳ ገንደ መሌ ሲንዳቡ (አመልሽ ብዙ ነው ሰፈር እንጂ አያስቆምሽም)

አን ደበሌ ሲንዋሙ. (እኔስ ከእንግዲህ ደግሜ አልጠራሽም)

በዘፈኑ ውስጥ የተጠቀሰችው “ደበሌ ዝማሙ” ማን እንደሆነች ለማወቅ አልቻልኩም (የሰው ስም መሆኑን የተረዳሁት ከሰለሞን አዘፋፈን ነው)፡፡ ሰለሞን እንዲህ ብሎ የዘፈነላት ከቤቷ የማትቀመጥ ሴት ናት፡፡ ሴትዮዋ ከሰፈር ሰፈር የምትንዘላዘለው ለብልግና አይደለም፡፡ ወሬኛ ሴት በመሆኗ ለወሬ ለቀማ ስትል ነው የምትዟዟረው፡፡ በመሆኑም amalli kee guddaadhaa ganda malee sindhaabu ማለትም “አመልሽ ትልቅ ነው ከሰፈር እንጂ አያስቆምሽም” ብሎአታል፡፡

አንጋፋው አርቲስት ተሾመ አሰግድም ከወለጋዋ የደምቢ ዶሎ ከተማ ነው የተገኘው፡፡ ተሾመ በጣም የሚታወቅበት የኦሮምኛ ዘፈኑ “ቢሻን አበያ” (የአባይ ውሃ) የተሰኘው ነው፡፡ አዝማቹ እንዲህ ይሄዳል፡፡

ቢሻን አበያ ያ ተሊላ ቶ

በሬዱ ኢንተላ ሙጫ ቢያ ኮ

ሲፉዴን ገላ ኮቱ ገረ ኮ

ይህ አዝማች በቀላል አማርኛ እንዲህ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡

እንደ አባይ ውሃ ንጹህ የሆንሽው

አንቺ ቆንጂቷ የሀገሬ ልጅ የሆንሽው

ነይልኝ ወደኔ ወስጄሽ ልብረረው፡፡

ሀይሉ ዲሳሳ እና ኤቢሳ አዱኛም የደምቢ ዶሎ ተወላጆች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የወለጋ ምድር እንደ ያህያ አደም፣ አብተው ከበደ፤ እልፍነሽ ቀኖ፣ዳግም መኮንን፣ ዳዊት መኮንን፣ ዳንኤል ታደሰ፣ ጅሬኛ አያና፣ ጌቱ ለሚ፣ ወዘተ… የመሳሰሉ የጥበብ ባለሙያዎችን አብቅሏል፡፡

——

የወለጋ ምድር ሰፊ ነው፡፡ ታሪኩም ጥልቅና ውብ ነው። እዚህ የቀነጨብኩት የባህር ጠብታ ያህል ነው፡፡ ህዝቡን ልትጎበኙት ብትሄዱ በፍቅር ይቀበላችኋል፡፡ ይህ ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ የሚታወቅበት ባህልና ልማድ ነው።

የዘመናችን የስውር ደባ ኤክስፐርቶች እና የጭካኔ አውራዎች ለፖለቲካ ዓላማቸው መሳካት ሲሉ በዚያ አካባቢ የሚፈጽሟቸው አሳፋሪና አሳዛኝ ግፎች የርሕሩሁን እና የባተሌውን የወለጋ ህዝባችንን ማንነት አይገልጹትም። ህዝቡን ለማወቅ የሚሻ ማንኛውም ግለሰብ ወደ አካባቢው ሄዶ እውነቱን በተግባር እንዲያየው ይመከራል።

ወለጋን እናውቀዋለን። እርሱም ያውቀናል። እኛ ወለጋ ነን። ወለጋም የኛ ነው። ሁላችንም የቦረና እና የበሬንቱ ልጆች ነን!

—-

(አፈንዲ ሙተቂ፡ “ቦረና እና በሬንቱ”፣ ከተሰኘው መጽሐፌ የተቀነጨበ: 2013፣ ገጽ 56-58)

ፎቶ: ውቢት ኢትዮጵያ (ውቢት አመንሲሳ)

Author: 21st Century Library & Information Technology Network [Information & Knowledge Dissemination Platform By Mulugeta Woldetsadik, Librarian/Information Professional at Hawassa University, Ethiopia]

Mulugeta Woldetsadik, Librarian/Information Professional @ Hawassa University, , Sidama Region, Ethiopia

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

%d bloggers like this: