በህግ አውጭው የወጣ አንድ አዋጅ ስጋና ደም ለብሶ በተጨባጭ ተፈጻሚነት እንዲያገኝ ብዙውን ጊዜ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያዎች ያስፈልጉታል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ያየን እንደሆነ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በተወካዮች ም/ቤት ከሚወጣው አዋጅ ይልቅ በየጊዜው ስለሚደነገጉት መመሪያዎች የተለየ ቅርበትና እውቀት አለው፡፡ በእያንዳንዱ አስተዳደር መ/ቤት ውስጥ የመንግስት ስራ የሚሰራው ‘በህጉ መሰረት’ ሳይሆን ‘በመመሪያው መሰረት’ ስለመሆኑ እውነትነት ያለው ሀቅ ነው፡፡
ስልጣን በሰጠው አዋጅ መሰረት እስከወጣ ድረስ በመመሪያ መስራቱ ባልከፋ ነበር፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ‘መመሪያ’ ሲባል ከስልጣን በላይ ለሆነ ድርጊት፣ ለህገ ወጥነትና ለኢ-ፍትሐዊነት የሚሰጥ የሽፋን ልብስ ነው፡፡ ዋና ችግሩ ከውክልና ሰጪው ከተወካዮች ም/ቤት ይጀምራል፡፡ በተለያዩ አዋጆች ላይ ለሚኒስትሮች ም/ቤትና ለአስተዳደር መ/ቤቶች በውክልና የሚተላለፈው ስልጣን እንደሰማይ የሰፋ ቢሆንም ጥያቄው የህግ የበላይነትና የህገ-መንግስታዊነት ሆኖ ተመክሮበት አያውቅም፡፡
ከዚህ ባሻገር አነስተኛ ስነ-ስርዓት ፈጽሞ አለመኖሩ መመሪያዎች ‘የስርቻው ስር ህጎች’ ሆነው እንዲቀሩ አድርጐታል፡፡ በተጨማሪም ህጋዊነታቸውንና በህግ አውጭው ከተሰጣቸው ስልጣን በላይ አለማለፋቸውን በተግባር የሚያረጋግጥ ውጤታማ የቁጥጥር ስልት አልተዘረጋም፡፡
መመሪያ የሌለው መመሪያ
አስተዳደራዊ ድንጋጌ አወጣጥ ስርዓት (Rule–Making Procedure) ግልፅነትና የህዝብ ተሳትፎን በማሳካት ረገድ ካለው ወሳኝ ሚና በተጨማሪ በዘፈቀደ በሚወጡ ደንብና መመሪያዎች አማካይነት የዜጐች መብትና ነፃነት እንዳይጣስ ከለላና ውጤታማ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ ነው፡፡ በአገራችን በሚኒስትሮች ም/ቤትና በአስተዳደር መ/ቤቶች የሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ለየትኛውም አይነት አስገዳጅ ስነ-ስርዓት አይገዙም፡፡ እስከ አሁን ድረስ ህግ አውጭው አንድ ደንብ በሚኒስትሮች ም/ቤት የሚወጣበትን ስነ-ስርዓት በአዋጅ ደንግጐ አላስቀመጠም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአስተዳደር መ/ቤቶች መመሪያ ሲያወጡ ሊከተሉት ስለሚገባ ስነ-ስርዓት የሚደነግግ አስገዳጅ ህግ የለም፡፡
ከመሰረታዊ የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች አንዱና ዋነኛው አስተዳደራዊ ድንጋጌ ቀላል በሆነ መንገድ ታትሞ መሰራጨት ያለበት መሆኑ ነው፡፡ በተግባር ያለው እውነታ እንደሚያሳየን መመሪያዎች በአስተዳደር መ/ቤቱ ውስጥ ተደብቀው የሚቀሩ የጓዳ ህጐች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ መመሪያዎች በ3ኛ ወገን ላይ አስገዳጅነት ቢኖራቸውም ሊታወቁና ሊከበሩ የሚችሉበት አንዳችም አማራጭ መንገድ የለም፡፡ ግለሰቦች እና ድርጅቶች በመመሪያው መሰረት እርምጃና ቅጣት ሲወሰድባቸው መመሪያዎቹ ባልታወቁበትና ባልታተሙበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህም የግልፅነትን መርህ የሚጥስ፣ ለሙስናና ከስልጣን በላይ ለሆነ ድርጊት እና በስልጣን አለአግባብ መገልገል በአጠቃላይ ለአስተዳደራዊ ብልሹነት የሚያጋልጥ አደገኛ ሁኔታ ነው፡፡ ማንም ዜጋ ላልታተመ፣ ለማያውቀው እና ሊያውቀው ለማይችል ህግ የመገዛት ግዴታ የለበትም፡፡
የመመሪያዎች አለመታተም ተፈጻሚነት (ውጤት) የሚያገኙበትን ጊዜ ለመወሰን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ለመሆኑ አንድ መመሪያ ውጤት የሚኖረው ከመቼ ጀምሮ ነው? በተለምዶ በመ/ቤቱ ኃላፊ ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ ውጤት ያገኛል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ያልተፈረመ መመሪያ በተግባር ተፈጻሚ የሚደረግበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ በአንዳንድ መመሪያዎች ላይ ደግሞ ተፈጻሚ የሚሆንበት ቀን በግልጽ ቢመለከትም የመ/ቤቱ ኃላፊ ፊርማ የለውም፡፡
በስነ-ስርዓት አለመኖር ምክንያት በየአስተዳደር መ/ቤቱ የሚወጡት መመሪያዎች ቅርጽና ይዘት ወጥነት አጥቷል፡፡ መመሪያ ለአውጭውም አካል ሳይቀር አስገዳጅ ህግ እንደመሆኑ አነስተኛ የሚባሉ ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ ይገባል፡፡ ለምሳሌ የመመሪያው መለያ ቁጥር፣ የተሻረ መመሪያ ካለ ቁጥሩና የወጣበት ጊዜ አንዲሁም ስልጣን የሰጠውን አዋጅ ቁጥርና አንቀጽ መጥቀስ ይገባል፡፡ እንዲሁም መመሪያው በምእራፍ፣ በክፍልና በአንቀጽ (ቁጥር) ተከፋፍሎ አስገዳጅነት ያለው ድንጋጌ ሊያስቀምጥ ይገባል፡፡ ይዘቱ ጥናት፣ ጥቆማ ወይም ምክር ወዘተ… መምሰል የለበትም፡፡
ህትመትና የሰበር ችሎት አቋም
መመሪያዎች በይፋ አለመታተማቸው በፍትሐብሔር እና የወንጀል ክርክሮች የሚረጋገጡበትን መንገድ ያወሳስበዋል፡፡ አውጭው አካል በተከራካሪነት ሲሰለፍ መመሪያ ጠቅሶ የሚያቀርበው ክርክር መመሪያውን እንደ አንድ የማስረጃ ዓይነት ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ከእርሱ በስተቀር ፍርድ ቤቱ ሆነ ባለጋራው ተከራካሪ ስለመኖሩ ሊያውቁ አይችሉም፡፡ ስራ ላይ መዋሉ ሊታወቅና ሊረጋገጥ የሚችለው የተባለውን መመሪያ እንዳወጣ የሚከራከረው የመንግስት ተቋም እንደ ሰነድ ማስረጃ ከመዝገቡ ጋር ማያያዝ ሲችል ነው፡፡
አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጠረው መመሪያውን ያወጣው አካል ተሳታፊ በማይሆንባቸው ክርክሮች ይዘቱ በአንደኛው ወገን መከራከሪያ ሆኖ ሲቀርብ ነው፡፡ ለምሳሌ ይህ ተከራካሪ ትክክለኛውን የመመሪያ ቁጥር መለየት ሳይችል ሲቀርና መኖሩ በተቃራኒ ወገን ሲካድ ፍርድ ቤቱ ሊከተለው የሚገባው አቅጣጫ ምንድነው? በመመሪያው መኖር ተጠቃሚነቱን ገልጾ የሚከራከረው ወገን የማስረዳት ግዴታውን ስላልተወጣ ክርክሩን ውድቅ ማድረግ አንደኛው አማራጭ ነው፡፡ ሆኖም ይህ አካሄድ ፍትሐዊነት ይጎድለዋል፡፡ መሰረታዊ የማስረጃ ህግ ደንቦችንም አያሟላም፡፡ አንድ ተከራካሪ አስገዳጅነት ያለውን የህግ ድንጋጌ ጠቅሶ ከመከራከር ባለፈ ‘ህግ እንደማስረጃ’ እንዲያቀርብ አይገደድም፡፡
‘መመሪያ ህግ ነው’ እስከተባለ ድረስ ካለበት ቦታ ማስቀረብ ዞሮ ዞሮ ፍርድ ቤቱ ጫንቃ ላይ ያርፋል፡፡ ሆኖም ያልታተመ መመሪያ ፍርድ ቤቶች ግንዛቤ እንዲወስዱበት አይገደዱም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ. 40804[1] በሰጠው የህግ ትርጉም፤
…በመንግስት የሚወጡ ሕጏች እና መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ ወዘተ በግልጽ የሚታወቁ እንደመሆናቸው ፍ/ቤቶች (ዳኞች) ግንዛቤ የሚወስዱባቸው ናቸው፡፡
ችሎቱ ያንጸባረቀው አቋም ዳኞች ያልተጻፈ እንዲያነቡ የማስገደድ ያክል ነው፡፡ እንደ ችሎቱ ከሆነ መመሪያ-ጠቀስ ክርክር በተከራካሪ ወገኖች ባይቀርብም ለውሳኔ አሰጣጥ የሚረዳ መመሪያ ካለ ፍርድ ቤቱ መኖሩን ማወቅ አለበት (በይግባኝ ደረጃ ደግሞ ማወቅ ነበረበት) ማለት ነው፡፡
የነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ዳኞች ያልታተሙ መመሪያዎችን ግንዛቤ እንዲወስዱባቸው አያስገድድም፡፡ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 3/1987 አንቀጽ 2/3/ ህግ ተርጓሚውን ጨምሮ ማናቸውም የፌደራልና የክልል የመንግስት አካላት እንዲሁም ህጋዊ ሰውነት ያገኘ ማንኛውም ድርጅት በነጋሪት ጋዜጣ የሚወጣን ህግ የመቀበል ግዴታ (shall take judicial notice of Laws published in the Federal Negarit Gazeta) አለበት፡፡ ስለሆነም ችሎቱ በሰ/መ/ቁ. 40804 ያንጸባረቀው አቋም ከነጋሪት ጋዜጣ ህጉ ጋር አይስማማም፡፡
ችሎቱ በከፊል የተለሳለሰ አቋም የያዘው በሰ/መ/ቁ. 83060[2] ሲሆን በመዝገቡ በሰፈረው የህግ ትርጉም መሰረት ክርክር የቀረበበት መመሪያ ይዘት ለውሳኔ አሰጣጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ፍርድ ቤት በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 145(1) እና 345(1)(ለ) ማስቀረብ ይገባዋል፡፡ ይህም ማለት አንደኛው ተከራካሪ መመሪያ ጠቅሶ ካልተከራከረ ወይም የመዝገቡ አካል እንዲሆን ካላሳሰበ በስተቀር የማስቀረብ ግዴታ አይኖርም፡፡ ፍርድ ቤትም በዚህ መልኩ ያልተነሳን ወይም በክርክሩ ያልተጠቀሰን መመሪያ በውሳኔው ከግምት ውስጥ ባለማስገባቱ ብቻ ውሳኔው በህግ ስህተት በይግባኝ ወይም በሰበር ሊሻር አይገባውም፡፡
የነጋሪት ጋዜጣ የህትመት ቅድመ ሁኔታ
ለመመሪያዎች አለመታተም ዋናው ምክንያት ልማድ እንጂ ህግ አይደለም፡፡ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ማናቸውም የፌደራልመንግስት ህግ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣ ያስገድዳል፡፡[3] አዋጁ መታተም ያለባቸውን የፌደራል መንግስት ህጎች በትርጓሜ አሊያም በዝርዝር አልለየም፡፡ ‘መመሪያ’ ከአዋጅና ደንብ ቀጥሎ አስገዳጅ ውጤት ያለው አንደኛው የፌደራል መንግስት ህግ እንደሆነ ክርክር አያስነሳም፡፡ ስለሆነም መመሪያዎች አለመታተማቸው የቆየ ልማድ እንጂ ህጉ በልዩ ሁኔታ ከህትመት ነጻ ስላደረጋቸው አይደለም፡፡
የአስተዳደር መ/ቤቶች በውክልና በተሰጣቸው ስልጣን የሚያወጡት አስተዳደራዊ ድንጋጌ በልዩ ሁኔታ ከህትመት ነጻ ባለመደረጉ የማሳተም ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ግዴታቸውን ካልተወጡ መመሪያዎቻቸው ውጤት ኖሯቸው ሊጸኑም አይገባም፡፡ ያልታተመ አዋጅና ደንብ ረቂቅ ሆኖ እንደሚቀር ሁሉ የመመሪያ ዕጣ ፈንታም ከዚህ አይለይም፡፡
የቋንቋ ጉዳይ
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መመሪያዎች ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹ የተጻፉት በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ነው፡፡ ባለስልጣኑ እንግሊዝኛውን ሲያስቀር ቋንቋውን አንብበው የማይረዱ በርካታ የውጭ አገር ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ዘንግቶታል ለማለት ይከብዳል፤ ችላ ብሎታል እንጂ፡፡ የዚህ የቆየ ልማድ ተገላቢጦሹን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እናገኛለን፡፡ ባንኩ በመመሪያ አወጣጥ ሂደት አማርኛ አይጠቀመም፤ እንግሊዝኛ ብቻ እንጂ፡፡ ይህ የልማድ አሰራር በግልና በመንግስት ባንኮች የህግ አተገባበር መሰረታዊ ችግር ላይፈጥር ይችላል፡፡ ሆኖም በህግ ተርጓሚው ላይ የሚፈጥረው ችግር ቀላል ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡ እንግሊዝኛ የማወቅ ያለማወቅ አይደለም ቁምነገሩ፡፡
በእንግሊዝኛ ተረቆ የተዘጋጀ ህግ በአማርኛ ወይም በሌላ የክልል ቋንቋ ሲተገበር ውስብስብ ችግር ያስከትላል፡፡[4] በአንደኛው የሚገኝ ቃል በሌላኛው አይኖርም፡፡ አንደኛው በአግባቡ የገለጸውን ሀሳብ አንዳንዴ ሌላኛው ያዛባዋል፡፡ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ እንዲታተም ያስገድዳል፡፡ በመካከላቸው የሚፈጠረውን የይዘት ልዩነት ለማስታረቅ አማርኛውን ብቻ ገዢ አድርጎ መጠቀም ውጤታማ አማራጭ ባይሆንም የአማርኛው የበላይነት ህጋዊ ዕውቅና አግኝቷል፡፡[5]
ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው በነጋሪት ጋዜጣ መታተም ያለባቸው ሁሉም የፌደራል መንግስት ህጎች ናቸው፡፡ ሆኖም በተግባር ሲታይ መመሪያዎች ለብቻቸው አፈንግጠው አይታተሙም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚዘጋጁበት መንገድ በውክልና ስልጣን የሰጣቸው ህግ የያዘውን መልክና ቅርጽ ሊያንጸባርቁ ይገባል፡፡ የህግ አውጭነት ስልጣናቸው ምንጭ የሆነው የተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ የሚጻፈው በአማርኛና በእንግሊዝኛ እስከሆነ ድረስ መመሪያዎችም ይህንኑ ተከትለው በሁለቱም ቋንቋዎች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በአንደኛው ቋንቋ ብቻ የተዘጋጀ መመሪያ አስገዳጅ ውጤት ሊኖረው አይገባም፡፡
የአስተዳደር መ/ቤቶች እየተከተሉት ያለው ዝብርቅርቅ የቋንቋ አጠቃቀም ከሚያስነሳው የህግ ጥያቄ በተጨማሪ ወደ አገራችን የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎችና ባለሀብቶች የአገሪቱን ህግ አክብረው ለመንቀሳቀስና ለመስራት የሚያደርጉትን ጥረት ከማገዝ ይልቅ ተጨማሪ ጫና ይፈጥርባቸዋል፡፡ ሆኖም የቋንቋ ጉዳይ ለሰበር ችሎት ብዙም አሳሳቢ ሆኖ አለመገኘቱ ሲታይ የተለመደው አሰራር ከህግ አውጭው አዋጅ በስተቀር የዳኝነት አካሉ ፍርድ መቼም የሚያስተካክለው አይመስልም፡፡
በሰ/መ/ቁ. 43781[6] ብሔራዊ ባንክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ ያዘጋጀው መመሪያ በአማርኛ ተተርጉሞ ባለመገኘቱ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውጤት ቢነፈገውም የሰበር ችሎት፤
በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሚወጡት የበታች ሕጎች… በተወሰነ ቋንቋዎች እንዲጻፉ የሚያስገድድ ሕግ የለንም፡፡
በሚል ምክንያት የመመሪያውን አስገዳጅነት ተቀብሎታል፡፡ ችሎቱ ‘ህግ የለም’ ይበል እንጂ ህጉስ አለ፡፡ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 3/1987 መመሪያዎች እንዲታተሙ ከዚያም አልፎ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች እንዲዘጋጁ ያስገድዳል፡፡ የአዋጁ ተፈጻሚነት በፌደራል መንግስቱ ህጎች ላይ እንጂ በተወካዮች ም/ቤት አዋጅ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ችሎቱ ‘መመሪያ በፌደራል መንግስት ህጎች ውስጥ አይጠቃለልም’ የሚል አቋም ከያዘ በመዝገቡ ላይ ‘መመሪያ ተላልፏል’ በሚል የወንጀል ክስ ቀርቦበት በይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ነጻ የተደረገውን ተጠሪ በወንጀል ድርጊት ጥፋተኛ ሊለው ባልተገባ ነበር፡፡
[1] አመልካች ዳንዲቦሩ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ እና ተጠሪ እነ ተክሉ ኡርጋ ኢደኤ /2 ሰዎች/ ጥር 26 ቀን 2001 ዓ.ም. ቅጽ 8
[2] አመልካች ገ/ማሪም ገ/መድህን እና ተጠሪ ጣዕመ ወ/ስላሴ ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ቅጽ 15
[3] የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 3/1987 አንቀጽ 2/2/
[4] የችግሮቹን መልክና ገፅታ በተለይ የተጠናቀሩት (Codified) ህጎቻችን በፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ መረቀቃቸው ያስከትሉትን ችግር ለመረዳት Roger Briottet “French, English, Amharic: The Law in Ethiopia.” Mizan Law Review 3 (2): 331-340 (2009) ይመለከቷል፡፡
[5] አዋጅ ቁ. 3/1987 አንቀጽ 2/4/ ይመለከቷል፡፡
[6] አመልካች የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እና ተጠሪ አቶ ዳንኤል መኮንን ሐምሌ 14 ቀን 2002 ዓ.ም. ቅጽ 10
SHARING IS CARING! Please Share Clicking On The below Social Network Buttons
Like this:
Like Loading...
You must be logged in to post a comment.