ለአብዲሳ አጋ ያልሆነችው ኢትዮጵያ ለማን ልትሆን ነው??? ….ያልተዘመረለት አባ ጅግሳ(አብዲሳ አጋ) ………VS ኢትዮጵያዊነት………………..(በጉማ ኦሮሚቲቻ)

(በዚህ ታሪክ የአብዲሳን ጀብዱ መተረክ አይደለም ያሻኝ)
.
አብዲሳ አጋ እምዬ ብሎ ካለላት ኢትዮጵያ ምን ነበር ያተረፈው? እስቲ በጥቂቱ እንየው፡፡
.
በኢጣልያ ተራሮች ላይ የተለያዩ ሀገር አርበኞችን አሰባስቦ ለ4 አመት ያህል ፋሽስቶችን አይቀጡ ቅጣት ሲቀጣ፣ስሙ ከመግነኑ አንጻር የኢጣልያ ጎረምሳዎች ፊታቸውን ጥቁር ቀለም እየተቀቡ እና መሳሪያ እየያዙ ጨለማ ለብሰው በየ ቤቱ እየገቡ” እኔ ሜጀር(ሻለቃ) አብዲሳ ነኝ”በማለት ዘረፋ ያካሂዱ ነበር፡፡ በመጨረሻም የያዛትን ሬጅመንት አሰልፎ በድል ግርማ ሮም ሲገባ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሰቅሎ ነበር፡፡ ቀጥሎም ዜግነቱን ለእንግሊዝ ወይንም ለአሜሪካ መንግስት እንዲያዛውር እና ባለበት የሻለቃ(ሜጀር)ማእረግ በሰራዊቱ ውስጥ እንዲቀጥል ሲጠየቅ”እንቢኝ “በማለቱ እንግሊዞች ከኢጣልያ ሹማምንት በመሻረክ “በአንኮና አውራጃ በሳንባሪኖ ወረዳ ላይ 32 ባላባቶችን ገድለሀል” ተብሎ 32 አመት ተፈረደበት፡፡
በአንድ የእንግሊዝ ፊልድ ማርሻል ማእረግ ባለው ሰው አማካይነት ይግባኝ ተጠይቆ ወደ ገንዘብ እነዲቀየርለት $18,000 ሲበየንበት በእንግሊዝ ዋስትና $7,000 ሀገሩ ገብቶ በየወሩ እንዲከፍል ተበየነበት፡፡ይህም የሆነው” አንቢኝ ለኢትዮጵያዊነት”ማለቱ ነው፡፡
.
ቁም ነገሩ ቀጣዩ ነው(ኢትዮጵያስ ለዚህ ጉምቱ ጀግና ምንነበር ያበረከተችለት እስቲ በጥቂቱ እንየው፡፡)
.
1,ግርማዊው ንጉሰ ነገስት ያን በኢጣልያ ምድር ላይ ነግሶ የነበረ ደቦል አምበሳ በገነት ጦር ትምህርት ቤት እንደ አዲስ ወታደር የጦር ታክቲክ እንዲማር ልከውት ፀጉሩን ተላጭቶ ከምልምል ወታደሮች(አዲስ ወታደሮቸች) ጋር እንዲሰለጥን አደረጉት፡፡
.
.በወቅቱ ንጉሰ ነገስቱ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ ቦሀላ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እያሰለጠኑ የነበሩት የእንግሊዝ መኮንኖች ነበሩ፡፡የአብዲሳ አጋን ታሪክ ልቅም አድርገው የሚያዉቁ ብቻ ሳይሆን በኢጣልያ በረሀዎች የተለያዩ ሀገራትን የነጻነት ተዋጊዎች ሲመራ እና ሲያዛቸው የነበረውን፣ የሰራቸውን ጀብዱዎችም ጭምር የሚያወቁት ያ…ሜጀር ማእረግ የተሰጠው ሰው ዛሬ ከምልምል ወታደሮች ጋር ጸጉሩን ተላጭቶ ተሰልፎ ቢመለከቱ ከሀዘናቸው የተነሳ ሜጀር ካዴት (ምልምሉ ሻለቃ)እያሉ ነበር እሚጠሩት፡፡
.
2,አብዲሳ ስልጠና ላይ እያለ የእንግሊዝ መንግስት የከፈለለትን ገንዘብ እንዲመልስላቸው በህግ ሲጠይቁት የወለዳቸው 2ልጆቹ እና መላው ቤተሰቡ በችግር አየተሰቃየ ይከፍል ስለነበር “ለምን ተፈጠርኩ” እስከማለት ደርሶ ነበር፡፡
.
3,ከማሰልጠኛው በምክትል መቶ አለቃ ማእረግ ተመርቆ ሲወጣ ከነበሩት 154 ሰልጣኞች 6ኛ ደረጃ ሁኖ የተመረቀ ቢሆንም ከእርሱ ጋር ተመርቀው የወጡት መኮንኖች ከ1939-53 አ.ም ባሉት አመታት የሻለቃ ማእረግ ላይ ሲደርሱ የኦሮሞው ልጅ አብዲሳ አጋ ለ14 አመታት በመቶ አለቃ ማእረግ ታግዶ ነበር የኖረው፡፡(ምናልባትም በዚህች ሀገር ታሪክ ይህን ያህል አመት ማእረግ የተነፈገ ይኖራል ብየ አልገምትም)
.
በኢጣሊያ በረሀዎች ነግሶ ለነበረው አባ ጅግሳ፣በዘመነ አጼውም ከኦጋዴን ክልል እንዳይወጣ የተበየነበት ሚመስለው ምስኪኑ ሰው ኢትዮጵያዊነቱ የከፈለችው ዋጋ ይሄ ነበር፡፡ የስራ ድልድል ላይ ጭምር ወደ 3ኛ ክፍለጦር እስታፍነት ቢላክም አብዲሳ የሚለው ስም ብቻ ለአፄያውያን አይመችም እና ወደ ኦጋዴን በረሀው ተመልሶ ተልኳል፡፡
.
1956 ኦጋዴን ቶጎ ውጫሌ ላይ የሶማሊ ተስፋፊ ወታደሮች በሙሉ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ እና በሜካናይዝድ የሚታገዝ ብርጌድ ጦር ወረራውን ሲከፍት በቦታው ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ሰራዊት የሚመራው አብዲሳ አጋ በቁጥር ከ300 የማያልፉ(አንድ ሻለቃ የማይሞላ ጦር) ወታደሮችን እና አሮጌ ጠመንጃዎችን በመያዝ ነበር ወደ መከላከል የገባው፡፡
.
ከ5-11ባለው ሰአት ውስጥ እልህ አስጨራሽ ውግያ ከተደረገ የሶማሌውን ሙሉ ብርጌድ ድል አድርጎ ከሙት የተረፈውን ከ900 በላይ የጠላት ሀይል(አንድ ሙሉ ሻለቃ) ሲማርክ የሸሹት አንዳችም መሳሪያ ይዘው አላመለጡም፡፡
.
ከተማረኩት መሳሪያዎች ውስጥ መድፎች፣ የአይሮፕላን ማውረጃ፣ Ptr እና BRDM ታንኮች፣የታንክ መስበሪያ ….. .እያልን መቁጠር ብንጀምር መጨረሻው ይረዝማል፡፡ አብዲሳ ግን በኦጋዴን በረሀ ከጠላቱ እየተናነቀ የእንግሊዝ መንግስት ከእስር እንዲለቀቅ የከፈለለትን ገንዘብ የህጻናት ልጆቹን ጉሮሮ አስርቦ እየከፈለ ቢጨርስም ኢትዮጵያ ግን ለአብዲሳም ሆነ ለሌሎች ብዙ አብዲሳዎች ዛሬም ያልከፈለችው ብዙ እዳ አለባት፡፡
.
ግርም ከሚሉኝ ነገሮች ውስጥ ደግሞ በአብዲሳ ዙርያ የተጻፉት ሁሉም ጽሁፎች የሌተና ኮሎኔል ማእረግ በንጉሱ እንደተሰጠው ነው የዘገቡት፡፡በጣም አሳፋሪ እና ከእውነት የራቀ ጉዳይ ሲሆን አብዲሳ ከሞተ ቦሀላ ነበር ደርግ ይሄ መሆን እንደሌለበት በማለት የኮሎኔል ማእረግ የሰጠው፡፡
.
አንድ ልቤን የነካኝ የዛሬ አመት የሶማሊ ክልል የኦሮሞ ተወላጆችን ሲያፈናቅል ለነዛ ለተፈናቀሉት ወገኖች የደረሱለት የራሱ ወገኖች ብቻ ነበሩ፡፡
.
አብዲሳ አጋ በምትለው ትንሽየ መጽሀፉ ላይም ” እኔን ከእዳ ለማውጣት አለንንልህ ያሉኝ ..” በማለት የዘረዘራቸውን ስሞች መልከት አደረኩ
.
ብላታ dheሬሳ አመንቴ
,ተሊላ ኢብሳ
,ይልማ dheሬሳ
,ደስታ ሮሮ,
ሳራ አያና,
ለሚ ቢርቢርሳ
,dheሬሳ ዳንኬ,
ኦላና ናትናኤል,
የሺእመቤት dheሬሳ…..እያለ ይቀጥላል፡፡
.
.
ለአብዲሳ ያልሆንሽ ኢትዮጵያ 👎
የአብዲሳ አጋ ¬አስገራሚ ታሪክ – ያልተዘመረለት የኢትዮጵያ ጀግና !! ( በስሜነህ ጌታነህ)
አብዲሳ አጋ በ1928 ዓ/ም የጣልያን ወረራ ወቅት ተማርኮ ወደ ጣልያን ከተወሰደ በኋላ ብርድ ልብሱን ቀዳዶ በመቀጣጠል በመስኮት አምልጦ በርካታ ጀግንነቶችን የፈጸመ የኢትዮጵያ ወታደር ነው። ኮሎኔል አብዲሳ አጋ የተወለደው በ1912 ዓ.ም ፣ ወለጋ ነበር።
በ12 ዓመቱ አባቱ በንዴት ወንድማቸውን በመግደላቸው ሲታሰሩ አብዲሳ አባቱን ለማስፈታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግም ሳይሳካ በሞት ተቀጥተዋል። በኋላም በ14 ዓመቱ የኢትዮጵያን ጦር በመቀላቀል ሀገሩን ማገልገሉን ሀ ብሎ ጀመረ። አብዲሳ ጦሩን ከተቀላቀለ ከሁለት አመት በኋላ የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል የዛተው ፋሺስት ሙሶሎኒ በድጋሚ ኢትዮጵያን ሲወር ሀገሩን ለመከላከል በ16 ዓመቱ ወራሪውን ጦር መዋጋት ጀመረ።
ውጊያ ላይ ባጋጠመው የመቁሰል አደጋ ህክምና ላይ ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ቤት በቁም እስር ላይ ነበር። በኋላ ጣልያን ኢትዮጲያን እንዲያስተዳድር በሾመችው ግራዚያኒ ላይ የመግደል ሙከራ ከተደረገ በኋላ አብዲሳ አጋ እና ሌሎች 37 የሚሆኑ የቁም እስረኞች ተጠርጣሪ ተብለው በከባድ ስቃይ እስር ቤት ከቆዩ በኋላ በወቅቱ የጣልያን ግዛት በነበረችው በሶማሊያ በኩል ወደ ጣልያን ተወስዶ በሲሲሊ ደሴት በሚገኝ እስር ቤት እስረኛ ተደረገ።
አልሸነፍ ባይነት መለያው የሆነው አብዲሳ ሁሊዮ ከተባለ ዩጎዝላቪያዊ የጦር እስረኛ ጋር በመተባበር ከባድ ጥበቃ ከሚደረግበት እስር ቤት ለማምለጥ ማሰላሰል ጀመረ። ተሳክቶለት ቢያመልጥ እንግዳ አገር እንደሚጠብቀው ቢያውቅም በነጻነቱ የማይደራደረው አብዲሳ የተሰጠውን የብርድ-ልብስ ቀዳዶ በመቀጣጠል በመስኮት በኩል አመለጠ።
ከዛ በኋላ ግን ሽሽት አልነበረም የጀመረው አብዲሳ። ከጥቂት ቀናት በኋላ በማታ ወደ እስር ቤቱ በመመለስ ጠባቂዎቹ ላይ ጥቃት በመፈጸም እስረኞቹን በመሉ ነጻ ማውጣት ችሎ ነበር። ያመለጡት እስረኞች ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች በወሰዱት መሳሪያ በመታገዝ የአማጽያን ጦር ያደራጁ ሲሆን ጦሩን እንዲመራም የመረጡት ጀግናውን አብዲሳን ነበር። ከዛም የተለያዩ የጣልያን ወታደራዊ ሠፈራዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ወራሪዎቹ ጣልያኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው የአርበኛ እንቅስቃሴ ያልተናነሰ ጥቃት በሀገራቸው ያጋጥማቸው ጀመር።
በአብዲሳ ጦር እጅግ የተረበሹት ጣልያኖችም በርካታ ስጦታዎችን ቃል በመግባት ውጊያውን እንዲያቆም እና የነሱን ጦር እንዲቀላቀል ለምነውት ነበር። አብዲሳ ግን ከፋሺስት ሥርዓት ጎን እንደማይቆም በማስረገጥ ጥያቄውን ውድቅ አደርጎ ጣልያኖችን በሀገራቸው ማስጨነቅ ቀጠለ።
በወቅቱ እየተጋጋለ የመጣው የጀርመን ናዚ ሥርዓት ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ሲጀምር ፋሺስት ሙሶሎኒ ከጀርመኖች ጋር ሲያብር እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ አገሮች የሕብረት ጦር መስርተው የሙሶሎኒን ጦር መውጋት ጀምረው ነበር።
በወቅቱ ይህ የሕብረት ጦር የአብዲሳን ዝና በመስማታቸው ጣልያንን ለማዳከም ለአብዲሳ ጦር የቁሳቁስ ድጋፎች ማድረግ ጀመሩ። በድጋፉ በመጠናከር ፋሺስቱን ሰራዊት ማርበድበድ የቀጠለው አብዲሳ የጣልያን ጦር ተሸንፎ ዋና ከተማዋሮም በአሜሪካን እና እንግሊዝ የሚመራ ጦር እጅ ስር ከወደቀች በኋላ የሚመራቸውን ከተለያዩ አገር የወጡ ወታደሮች በሙሉ ክንዳቸው ላይ የኢትዮጲያን ባንዲራ እንዲያስሩ በማድረግ የሃገሩን ባንዲራ እያውለበለበ ሮም ከተማ ሲገባ በአለም አቀፉ ህብረት ጦር ትልቅ አቀባበል ተደርጎለት ነበር።
ከዛም በኋላ ከተጨማሪ ወታደሮች ጋር በአለም አቀፉ ህብረት ስር የሚመራ ጦር መሪ በመሆን ጀርመንን ለማሸነፍ በሚደረገው የመጨረሻ ውጊያ ላይ ተሳትፎ ግዳጁን በሚገባ በመወጣት የኢትዮጲያን ባንዲራ ከእጁ ሳይለይ በርካታ የጀርመን ከተሞችን ነጻ ማውጣት ችሎ ነበር። ከጦርነቱ መገባደድ በኋላም የእንግሊዝ፣ የካናዳ እና የአሜሪካ መንግሥታት ጦራቸውን ተቀላቅሎ እንዲቀጥል በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችን አቅርበውለት ነበር። አብዲሳ ግን ኢትዮጵያ ምንም ያህል ድሃ ብትሆንም ሕዝቡን እና መንግሥቱን ጥሎ እንደማይሄድ አስረግጦ በመናገር ጥያቄውን ሳይቀበል ቀረ።
ተቀላቀለን የሚለውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ያልተዋጠላቸው አንዳንድ የሕብረት ጦሩ አባላት ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በወንጀል ከሰው አብዲሳን እስር ቤት አስገብተውት ነበር። በኋላም እስሩ ወደ ገንዘብ ቅጣት ተቀይሮ ገንዘቡ ተከፍሎ አብዲሳ ለዓመታት ወደተለያት ሀገሩ በክብር ተመለሰ። ከዛም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በክብር ከተቀበሉት በኋላ በጊዜው የመከላከያ ሚኒስቴር ወደነበሩት ራስ አበበ አረጋይ መርተውት ነበር።
ሚኒስቴሩ ውደመሩት ወደ ሆለታ ወታደራዊ ሠፈር የገባው አብዲሳ አነስ ባለ ወታደራዊ ቦታ የተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ ለጉብኝት የሚመጡ የውጭ ሀገር የጦር መሪዎች ስለ ዝናው ሲያወሩ የሰሙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ቤተ መንግሥታቸው በማምጣት በኮሎኔልነት ማዕረግ የንጉሡ ጠባቂ ሆኖ አድርገው ሾሙት። እስከ ንጉሣዊ ሥርዓቱ መውደቅ ድረስ በቦታው ያገለገለው አብዲሳ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።