60 ዓመታትን የተሻገረ ምጥ
‹‹እንዘጭ-እንቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ›› በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃውን የመስፍን ወልደማሪያም (ፕ/ር) መፃፍ ምረቃ መነሻ በማድረግ ባሳለፍነው ቅዳሜ በኬምብሪጅ የተዘጋጀው ፕሮግራም ይህን ሐሳብ ለመወርወር መነሻ ሆነኝ፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ በቦስተን እና አካባቢው የሚገኙ የፕሮፌሰሩ አድናቂዎች፣ ሀሳባቸውን ለመሟገት የመረጡ የአገራችን ሰዎች፣ የተገኙ ሲሆን ሰማኸኝ ጋሹ (ዶ/ር) – የሰብዓዊ መብትና የዓለም አቀፍ ሕግ አስተማሪና ተመራማሪ፣ አቶ ገለታው ዘለቀ – የኢትዮጵያ ሪሰርችና ፖሊሲ ተቋም ጸሀፊ፣ የህግ ተመራማሪው እና ጦማሪው ዘላለም ክብረት (በሃርቫርድ ዩንቨርስቲ ሀትቺንስ ማዕከል ፌሎው) በመፅሐፉ ዙሪያ ያላቸውን አጭር አስተያየት በእለቱ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ውጪም ከቦስተን ውጪም እንደ ደረሰ ጌታቸው (ዶ/ር) – የአርበን ሶስዮሎጂ አስተማሪና ተመራማሪ ያሉትም ከኒው ዮርክ በመምጣት ተሳትፈውበታል፡፡ በአደባባይ ምሁርነታቸው፣ በሰብኣዊ መብት ተሟጋችነታቸው፣ በፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ አቋማቸው ፕሮፍ የብዙ ሰዎች ምሬትን፣ የሶስት ሥርዓት ተግሳፅን ሆነ እስርን ተቋቁመው በደረሰባቸው ያልተገባ ቅጣት ሳይመረሩ የልባቸውን ያለፍርሃት እየተናገሩ፤ ላመኑበት ነገር በፅናት በመቆም አስፈላጊ ሲመስላቸውም ብዙዎች አንድ የሆኑበትን ሐሳብ ሳይቀር ብቻቸውን ሚያስቀር ቢመስል እንኳ ሐሳባቸውን ለማንጸባረቅ ወደ ኋላ ባለማለት (ለዚህ ምሳሌ ብዙዎች የሚያውቁት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ኤርትራውያን ከአገር እንዲባረሩ ሲደረግ እርሳቸው ይህን የመንግስት ውሳኔ በመቃወም በአደባባይ ይህን አቋማቸውንም በመግለፁ ብቻ ሳይገቱ ያልተገባ ባሉት የመንግስት ውሳኔ ኤርትራውያን ከቤት ንብረታቸው እንዳይፈናቀሉ የሚችሉትን ሁሉ በተግባር ያደረጉ ናቸው፡፡ የዚህን ጉዳይ ዝርዝር ወደፊት ራሳቸው ያስነብቡን ይሆናል፡፡)
ከ85 ዓመታቸው በኋላ ብዙዎች ምን ያደርጉ ይሆን? የሚለውን መጠየቁ ለፕሮፍ ለማይዝለው ብእራቸው አድናቆትን ለመቸር እንድንነሳሳ ይገፋፋል፤ ከዚህ ውጪ ግን ዛሬም ሐሳባቸውን ለሚሞግት እሳቸው “እንዴት ተነካሁ?” ባይነት አይዳዳቸውም፣ ደርግ ሥልጣኑን እንደተቆናጠጠ ለሚሰጡት የተለየ ሐሳብ ሹማምንቱ ‹‹ሽማግሌው›› እያሉ ሐሳባቸውን ከመቀበል ወደኋላ ይሉ የነበር ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ዓመታት በኋላም ይበጃል ያሉትን ሐሳብ ከማጋራት አልተገቱም፡፡ በመጻህፋቸው ምረቃ ወቅት ባቀረቡት ማብራሪያ ‹‹ ከልጅነቴ ጀምሮ የነበረኝ ፍላጎት በኢትዮጵያ የቤተ ክህነት ትምህርት ለመግፋትና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በጥልቀት ለማጥናት ነበር፤ ነገር ግን ከእኔ ቁጥጥር ውጭ በሆኑ ምክንያቶች የልጅነት ምኞቴ ሳይሳካልኝ ቀረ፤ የቤተ ክህነቱን ትቼ ተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ገባሁ፤ ከዚያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሲከፈት ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች አንዱ ሆንሁ፤ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለአንድ ዓመት ያህል ቆይቼ በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆንሁ፤ ከዲሬክተርዋ ከወይዘሮ ስንዱ ጋር ተጋጨንና ከእተጌ መነን ወጣሁ፤›› መጋጨት ልማዴ ነው መሰል ብለው ፈገግ አስብለውናል፡፡ በተለይ ከዚህ በኋላ ፕሮፍ አጋጣሚ ሆኖ ወደህንድ ለትምህርት መሄዳቸው ራሳቸውን ለማወቅ የቻልበት ሁኔታን ስለመፍጠሩም ያወሳሉ፡፡
‹‹ በህንድ አገር የመጀመሪያውን ሌላ አገር አየሁ፤ ህንድ ከሁለት መቶ በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩበትና ከነዚህም ሃያ ሁለት የሚሆኑት የየራሳቸው ፊደል ያላቸው መሆናቸውን ስረዳ የእኔን አገር ትንሽነት ገለጠልኝ፤ ነገር ግን የህንድ ሕዝብ ከአሥራ ሦስተኛው ምዕተ-ዓመት አስከአሥራ ስምንተኛው ምዕተ-ዓመት በተለያዩ የእስልምና ኃይሎች ስር ወድቀው ከቆዩ በኋላ ከአሥራ ስምንተኛው ምዕተ-ዓመት በኋላ ደግሞ እአአ አስከ1 947 የብሪታንያ ቅኝ ግዛት ሆነው ቆዩ፤ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሌም በነጻነት በመኖሩ ልቤ ኮራ፡፡›› ይሉናል፡፡ ኩራታቸው ግን እንዳለ አልቆየም፡፡ ቀስ እያለ የተፈጠረባቸውን ስሜት እንዲህ ይገልፁታል፡፡ ‹‹እየቆየሁ፣ እያደግሁና ብዙ ነገሮችን እየተገነዘብሁ ስሄድ የኢትዮጵያዊነት ኩራቴ በደሀነት ብል እየተበላ ተናደብኝ፤ በዚህ ጊዜ በአንድ በኩል በታሪካዊ ኩራት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በኑሮ ደሀነት ተወጥሬ የተያዝኩበት ሀሳብ የኢትዮጵያን ሕዝብ ምን ይዞት ነው በሥልጣንና በሀብት ድልድል ለማደግና ለመሻሻል ያልቻለው? የሚል ጥያቄ ነበር፤ ይህ ጥያቄ አእምሮዬን ቀስፎ ይዞት ኩራቴ ወደ ቁጪት ተለወጠ፤ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማወቅ በትሬንታ ኳትሮ፣ በባቡር፣ በእግሬና በበቅሎ፣ በላንድሮቨር ተራራውን ስወጣ፣ ቁልቁለቱን ስወርድ ሁሌም የሚነዳኝ ይህ ጥያቄና ቁጪቱ ነበር፡፡›› ይህ ቁጭት በተለይ ወደ ብስጭት እንዲያመሩ ያደረጋቸው ሲሆን ዩኒቨርሲቲም በሚስተምሩበት ጊዜ ኢትዮጵያ ወደኋላ መቅረትዋ ብቻ ሳይሆን ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብም ወደኋላ መቅረት የተመቸው እየመሰለኝ እበሳጭ ነበር፤ አሁንም ያበሳጨኛል፡፡›› ሲሉ ከወጣትነት እስከ አዛውንትነት ዕድሜያቸው ከውስጣቸው ያልተለየውን በወገናቸው ተቆርቋሪነት ያደረባቸውን ስሜታቸውን ይናገራሉ፡፡
ከልጃቸው መቅደስ (ዶ/ር) ጋር እኔና ዘላለም ልንጠይቃቸው በሄድንበት ወቅት ከዘመን አቻቸው በእጅጉ የተለየ የሚያደርጋቸው ትጋት ሳይለያቸው፤ ላፕቶፓቸው ላይ የአጋሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያ እየተከታተሉ፣ አለኝ ያሉትንም ሐሳብ (ሶስት አስርተ አመታት ያለፈው የጡረታ ዘመናቸው ሳይገድባቸው) እየወረወሩ ነበር፡፡ በዚህ የእረፍት ዘመናቸው የጤናቸው ሁኔታ ከፍተኛ እንክብካቤን እና እረፍት የሚሻ ሆኖም ሳለ ከማህበራዊ ሚዲያውም ተሳትፎዋቸው ባለፈ ይህንኑ መፅሐፍ ለማዘጋጀት መንስኤ የሆናቸውን ነገር ሲያወሱም ‹‹ጡረታ ከወጣሁ ሠላሳ ሁለት ዓመቶች ያለፉ መሰለኝ፤ ያም ሆኖ፣ በጡረታ ላይ ሆኜም በወጣትነቴ በውስጤ የተፈጠረው ጥያቄ አልለቀቀኝም፤ ይኸ ጽሑፍ የዚህ ውጤት ነው፤ የመጽሐፉ ዋና ይዘት ከብዙ ዘመናት በኋላ ከዚህ ጥያቄ የተወለደ ግኝት ነው፤ በከባድ ምጥና ጭንቀት የተወለደ ሀሳብ ነው፤ አሁን በአለሁበት ሁኔታ ሀሳቡን ለማሰራጨት አይመችም፤ አስተማሪ ብሆን በውድም ሆነ በግድ ተማሪዎቼን እንደአብሽ እግታቸው ነበር፤ አሁን በአለንበት ሁኔታ ግን ሰፊና ነጻ የውይይት መድረክ ባለመኖሩ ሀሳቡ ፋይዳ ያለው እርምጃ ይኖረዋል ብዬ አላምንም፤ ሆኖም ትንሽም ቢሆን በመኮርኮር ለማንቃት ከተቻለ እንሞክር፡፡›› ከሚል ሐሳብ በመነሳት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹እንዘጭ-እንቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ›› በሚል ርዕስ ያሳተሙት ዳጎስ ያለ መፅሐፍ ያዘጋጁበትን ምክንያት ሲገልፁ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ለብዙ የማኅበረሰባዊ ጥናቶች፣ በጂኦግራፊና በታሪክ፣ በማኅበረሰብ ጥናት፤ በሥልጣንና በኑሮ ዝርዝር ጠቃሚ ጥናት ሊካሄድበት የሚችል ርእስ መሆኑን በማውሳት ነው፡፡ አንደ እናት ከ9 ወር በኋላ እርግዝና ልጇን ባስቸጋሪ ምጥ እንደምትወልደው ሁላ ፕሮፍም ከወጣትነታቸው ጊዜ አንስቶ ከአእምሮዋቸው ሲብላላ የነበረውን ጥያቄ እና ቁጭት መሰረት በማድረግ ከረጅም ጊዜ ምጥ በኋላ መፅሐፍን ስለመሰናዳቱ በአጭሩ ያወሱት ‹‹ የአንድ ሰው የረጅም ጊዜ ምጥና ጭንቀት ነው፤›› በማለት ነበር፡፡
በዚህ መፀሃፋው ፕሮፍ በምልዓት ከ’አድዋ1888’ ተነስተው፣ በ’ማይጨው 1928’ የተከሰተውን አውስተው፣ በጂጂጋ 1968 የተከወነውን ነገር እያወሳሱ አሁን ያለንበት ጊዜ ላይ ያለውን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ታሪካዊና ሌሎችንም ኩነቶች በስፋት ይዳስሳሉ፡፡ በተለይ አንባገነናዊ ሥርኣቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ሂስን በስፋት ህረተሰቡን መሰረት አድርገው ጭምር ዝርዝር ትንታኔ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከወትሮው በተለየ የሚያስብል በስፋት የዳሰሱት ማድፈጥ ሲሉ የሚገልፁትን ሐሳብ ነው፡፡ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተም እርሳቸው የመጽሐፉ እንቡጥ ሀሳብ <<ማድፈጥ>> ስለመሆኑ አውስተዋል፡፡ ‹‹ ማድፈጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ያለው የኃይሉም፣ የድካሙም መግለጫ ነው፤ የድካሙ መግለጫ እንደመሆኑ ጥቃት ይፈጸምበታል፤ የኃይሉ መግለጫ እንደመሆኑ ዕድሉን ጠብቆ በቀሉን ይወጣበታል፤.. ማድፈጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በግፍ አገዛዝ ላይ የሚፈጽመው እስከዛሬ ያልታወቀ የበቀል ዘዴ ነው፤ምርጫ ሲያሳጡት ሕዝቡ የሚወስደው የራሱ ምርጫ ነው፤›› በማለት የሚገልጹትን ሐሳብ መነሻ በማድረግ ፕሮፍ በዚህ መጽሀፋቸው ማድፈጥ ምንድን ነው?፤ የማድፈጥ ባሕርያት፣ ማድፈጥ የግለሰብ ሀሳብ ነው ( ገፅ 21) ማድፈጥ ምሥጢር ነው፤ መለገም የማድፈጥ አንዱ የማጥቂያ መሣሪያ፣ የማድፈጥ የመጨረሻ ዓላማ፣ የማድፈጥ ውጤት – በተግባር (ገፅ 24)፤ የማድፈጥ ጉዳት (ገፅ 26) በሚሉ ንዑስ ርእሶች ጉዳዩን በጥልቀት በመተንተን ያቀርቡታል፡፡ ይሄ ጉዳይ አጠቃላይ አገራዊ ማህበራዊ ጉዳዮችን በጥልቀት የሚያጠኑ ሰዎች በርግጥ ይህ ፕሮፍ ያነሱት ሐሳብ ያለውን ድርሻ በስፋት በማጥናት ለለውጥ የሚያግዙ ሐሳቦችን ቢያመነጩ ዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብን በመፍጠር አምባገነናዊ ሥርዓትን ለመቅጨት የሚደረገውን ጉዞ ባፋጠነ ነበር ያሰኛል፡፡
የስም ማውጫን ጨምሮ በ260 ገፆች ተቀንብቦ የተሰናዳው ይህ መጽሀፍ እንዘጭ!-እምቦጭ! ከመሠረቱ፣ መነሻ ጥያቄዎች፣ መድረሻችን ከመነሻችን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ና ሕጋዊ ሥርዓት፣ ግፍና ግፈኛ፣ የጉልበተኛነት አዝማሚያ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኃላፊነት፣ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ ሕግና ማኅበረሰባዊ ኑሮ፣ ሕገ መንግሥትና ሕግ አስከባሪነት፣ የሀሳቦች መምከን
እንዲሁም ባህላዊና ዘመናዊ ትምህርት (ገፅ 167)፣ ከሕገ አራዊት መላቀቅ (ገፅ 199) ዋናዎቹ የኢትዮጵያ ችግሮች (ገፅ 210) ጨምሮ የማይዳስሱት አገራዊ ጎዳ እና አጀንዳ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌም ‹‹እንዘጭ!-እምቦጭ!›› እያሉ የሚገልፁዋቸውን አንዳንድ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ጨምሮ (ከገፅ 132 እስከ 142 ያለውን ይመለከተዋል) ዋና ዋና ሕዛባዊ ድርጅቶች በሚለው አብይ ርዕስ ዙሪያ ደግሞ- የሠራተኞች ማኅበራት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፣ የሥነ ጥበባት ባለሙያዎች፣ የፖሊቲካ ቡድኖች፣ ጋዜጠኞች፣ የመንፈሳዊ መሪዎች ተሳትፎን የተመለከቱ ዝርዝር ሀሳቦች ያወሳሉ፡፡
በስፋት ለሚያነሱት ችግሮችም መፍትሄ ይሆናሉ የሚሉዋቸውን ሐሳቦች ከዳበረ ልምዳቸው፣ በግል ካደረጉት ጥናት እና ምርምር፣ ከዳበረ የንባብ ባሕላቸው፣ በአካል ከተሳተፉበት ገጠመኖች እና ተሞክሮዎች በመነሳት – እንዴት ሽግግር (ገፅ 72)፣ ሰው መሆን ያቃታቸው ፖሊቲከኞች (ገጽ 78)፤ አንድነት በልዩነት፣ ልዩነት በአንድነት (ገጽ 85)፤ ከፖሊቲካ በፊት ሰው መሆን (ገጽ 87) ከአገዛዝ ወደ ፖሊቲካ (ገጽ 92)፣ የሕዝብ አቅመ-ቢስነትን ለማጥፋት (ገጽ 244) በሚል በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭቆናንና በደልን የሚመለከተውና የሚቀበለው በግል፣ ለየብቻው ሆኖ ነው፤ የሚልን ሐሳብ በመፅሐፋቸው ላይ በስፋት የሚያወሱት ፕሮፍ ይህም በጋራ በመተባበር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳይገነባ ከማድረጉ ባለፈ ‹‹በሚደርስበት በደልና ጭቆና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቂም ይይዛል፤ በደሉ፣ቂሙ፣ በቀሉ የግል ነው፤ ቂም የእያንዳንዱ ሰው ምሥጢር ነው፤ ስለበደሉና ስለጭቆናው በውስጡ የተከማቸውን ቂምና የሚመኘውን በቀል ማንም እንዲያውቅበት አይፈልግም፡፡›› ይሉ እና የማድፈጥ ዓላማው በቀል መሆኑን ያወሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ማድፈጥም ሆነ በቀል ሰላምን አይሰጡትም፤ በዝምታ ማድፈጥ እንዳይታገል ያደርገዋል፤
በምሥጢር የሚይዘው ቂም እውነተኘ ችግሩን በጋራ ለመፍታት አያስችለውም፤ በማለት በዝርዝር እንደ አንድ አገር ሕዝብ አለብን የሚሉትን ችግር ይዘረዝራሉ፡፡
‹‹የሄድንበትን እንሄድበታለን?›› የሚል ጥያቄን በማስቀደም ፕሮፍ የመጽሐፍቸው ዓላማ ያለፈውን ለመውቀስ ሳይሆን ‹‹ያለፈ የሚመስለውንና አሁንም በውስጣችን ያለውን እውነት ማውጣትና ማሳየት፣ መናገር ነው፤ ያለፈው ትውልድ የፈጸመውንና አሁንም በእኛ ውስጥ ያለውን ማውጣት ያለፈውን መውቀስ ሳይሆን ያለውን ለማጽዳት መሞከር ነው፤ የኔ ዓላማ ያለውና ወደፊት የሚመጣው ራሱን ለማስተካከል ራሱን በአለፉት ውሰጥ አይቶ ራሱን እንዲታዘብ ነው፤ራሱን ታዝቦ ራሱን እንዲለውጥ ነው፤›› ሲሉ ይገልፁታል፡፡ ‹‹ታሪክ ራሱን ይደግማል›› እንደሚባለው ብሂል በአገራችን በተደጋጋሚ አሳዛኝ ነገሮች ራሳቸውን ደግመዋል፡፡ በአገዛዞቹ አምባገነንነት የሚከሰቱትን እነዚህን አላስፈላጊ እልቂቶች ለማስቀረት ካለፈው መማሩ ግድ ነው፡፡ ለዚህም የሶስት ሥርዓቶችን ኩነት ተሸግሮ የተሰናዳው የፕሮፍ መጽሀፍ የላቀ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
ፕሮፍ – << ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ መሆኑን አውቃለሁ፤
አልቀበር እንጂ እኔኮ ሞቻለሁ፤ >> የሚለውን ግጥማቸውን ባስቀደሙበት እና ‹‹ዋናዎቹ የኢትዮጵያ ችግሮች ያሉትን በዘረዘሩበት ምዕራፍ ውስጥ ‹‹ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ዋናዎቹ የኢትዮጵያ ችግሮች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተደነገጉ ናቸው፤ … የሕይወት (በሕይወት የመኖር መብት)፤ የአካል ደኅንነት መብት፤ በነጻነት የመኖር መብት፤ የእኩልነት መብት፤ የሃይማኖትና የእምነት ነጻነት፤ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት፤ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት … ›› የመሳሰሉትን ጨምሮ መሰረታዊ የዜጎች መብት የተሰኙት አንቀፆችን በመዘርዝር ‹‹ እነዚህን ነጻነቶችንና መብቶችን የሚያውጁ አንቀጾች የኢትዮጵያ ዋና ችግሮች ናቸው፤›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ (ዝርዝሩን ከገጽ 85 አንስቶ ማየት ይቻላል፡፡)
ከላይ ከተወሳው ያልተለመደ ሐሳባቸው ወጣ በማለትም በእኔ በአንድ ሰው ዕድሜ የፋሺስት ኢጣልያንን አገዛዝ፣ የአጼ ኃይለ ሥላሴን አገዛዝ፣ የደርግን አገዛዝ፣ የወያኔን አገዛዝ አይቻለሁ፤ እነዚህ ሁሉ አገዛዝ በመሆናቸው አንድ ናቸው፤ ነገር ግን ባሕርያቸው የተለያየ ነው፤ የሚሉት ፕሮፍ ‹‹ የኢትዮጵያ ሕዝብ በግፈኛ አገዛዝ ስር ለምዕተ-ዓመታት የቆየው እንዴት ነው? በብዙ ምዕተ-ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥልጣንን ለመግራት ሕግን አውጥቶ በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሥርዓተ መንግሥት ማቋቋም እንዴት አቃተው?›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ አክለውም ‹‹ ሲወርድ ሲዋረድ አሁን ባለንበት ዘመን ድረስ የአንድ ሰው አገዛዝ ወይም አንድ ሰው ከጥቂት ሎሌዎቹ ጋር ሆኖ አድራጊ-ፈጣሪ፣ ቆራጭ-ፈላጭ ሆኖ ሕጋዊ ኃላፊነትም ሆነ ተጠያቂነት በሌለው አገዛዝ ለብዙ ምዕተ-ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተሰቃይቷል፤ ግፈኛውን እያደፈጠ ቢደፍቅም ሥርዓቱን ለመለወጥ አልቻለም፤ ሥርዓቱም በተከታታይ ከሚደርስበት የውርደት ውድቀት ተምሮ ሕግን ተመርኩዞ ራሱን ለመለወጥ አልደፈረም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጭቆና አገዛዝን በማድፈጥ ለመጣል የሚያደርገው ቆራጥ እርምጃ ትክክለኛና ሕጋዊ ሥርዓትን ለመትከል ለምን አልዋለም? የግፍ አገዛዝን እያደፈጡ መጣል ወይም መንቀል አዲስና ሕጋዊ ሥርዓትን ወደመትከል ያልተሸጋገረበት ምክንያት ምንድን ነው? መጣል ወይም መንቀል ከመትከል የቀለለ ሆኖ የታየው ለምንድን ነው? ለመንቀል የሚያስፈልገው ለየብቻ ቂምን ቋጥሮ ግፈኛውን የሚቋቋም አጋር ሲመጣ ማጀብ ብቻ ነው፤ መትከል ግን የብዙ ቁም-ነገሮችን መሟላት ይጠይቃል፤ ይህንን ጉድለት ቆይተን እናየዋለን፡፡ እነዚህን ጉድለቶች በማን ላይ እንጣላቸው? በመሪዎች ላይ ነው? ወይስ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ? ወይስ በሁለቱም ላይ?›› በማለት ለምላሹ ይተጋሉ፡፡
በእርግጥም እርሳቸው ያነሱት ለመሰረታዊ ለውጥ የሚረዳ ሐሳብ እንዳለ ሆኖ መጽሀፍ በርግጥ ብዙ ነገሮችን ለውይይት ከመጋበዝ ባለፈ ብዙ ጥያቄዎችንም የሚያስነሳ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ጥቂቶቹ በመጽሀፍ አዘጋጅ ሊመለሱ የሚገባቸው ብዙዎቹ ግን በፖለቲካ፣ በታሪክ እና በማህበራዊ ሳይንስ ዙሪያ የተሰማሩ ተመራማሪዎች ተገቢውን ጥናት በማድረግ የመፍትሄን ሐሳብ ሊያመነጩበት የተገባ ነው፡፡ (በሌላ ግዜ እንዚህን ጥያቄዎች ዝርዝር ከተሳካልኝ የፕሮፍን ሀሳብ በማከል ጭምር ልመለስበት እሞክራለሁ፡፡ ለጊዜው ግን መጽሀፋ ገና ሰው ዘንድ በስፋት ባለመድረሱ ከዚህ የበለጠ ማውሳቱን አልመረጥኩም፡፡)
ፕሮፍ በሕይወት ዘመናቸው የገጠማቸውን ነገር በማውሳት እንደ ማስጠንቀቂያ ያወሱትን ሐሳብ በማከል ነገሬን ልቋጨው፡፡ ‹‹ ነገ የወጣቶች ነው፤ ትናንት የሽማግሌዎች ነበር፤ ይባላል፤ በትክክልና በጥሞና ካልታሰበበት ይህ የተለመደ አባባል ስሕተተኛ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው፤ እኔ አርባ ዓመት አልፎኝ ወጣት በነበርሁበት ጊዜ ኢትዮጵያን የሚያሽከረክሯት ሽማግሌዎች ነበሩ፤ ‹‹ይሄ ልጅ›› ይሉኝ ነበር! አርባ አራት ዓመት ግድም ሲሆነኝ ኢትዮጵያን የሚያሽከረክሯት ወጣቶች ሆኑና ‹‹ይሄ ሽማግሌ›› ይሉኝ ጀመር! ‹‹ይሄ ልጅ›› ሲሉኝ ልሠራ የምችለውን ብዙ ነገር የማልችል አደረጉኝ፤ እንደዚሁም ‹‹ይሄ ሽማግሌ›› ሲሉኝ በጣም ደካማና ኋላ-ቀር አደረጉኝ፤ ራስን ከፍ ለማድረግ ሲባል ሌላውን ዝቅ ማድረግ የሥልጣን ጥመኞቹን የሚረዳ ቢሆንም ማኅበረሰቡን በጣም ይጎዳል፡፡››
መጻፉን ለመግዛት የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ መጠቀም ይችላሉ፡፡ https://www.mesfinwoldemariam.org/