
ዶ/ር ገረመዉ ኃይሌ
በአዲስ አበባ ዩነቨርሲቲ ፤የአዋሳ እርሻ ኮሌጅ ዲን እኝህ ነበሩ
The late Dr. Geremrew Haile
ከ1972-1983 ዓ.ም.
የአብዮቱን ፍንዳታ ከ40 ዓመት በኃላ ስናስታውስ ሁላችንም በአብዮቱ ሂደት ውስጥ ያየናቸውን ገጠመኞች ማስታወሳችን አይቀርም። በተለይም የ17 ዓመቱን የደርግ አገዛዝ የሁላችንም ትዝታ ነው። ከፊሎቻችን የተደሰትንበት፣ በተስፋ የፈነደቅንበት፣ ሌሎቻችን ደግሞ ያዘንበት፣ የተጎዳንበት፣ ወቅት ነበር። የዝብርቅርቅ ዘመን። በዚህ በደርግ ዘመን ውስጥ የብዙዎቻችን ሕይወት የለወጡ ክስተቶች ነበሩ። አንዳንዶቹ ገጠመኞች አስቂኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ደግሞ የሕብረተሰቡን የውስጥ ስሜትን የሚገልጹ ነበሩ። በእኔ አመለካከት እነዚህ በቀልድ፣ ወይም በተረት ወይም ደግሞ በአባባል የሚገለጹ ብሶቶች ናቸው የደርግን ዘመን በደንብ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩት። ታሪክን ሠሪው ሰፊዉ ሕዝብ ነውና ከእሱ በላይ ታሪክን ገላጭ አይኖርም።
በደርግ አገዛዝ ዘመን በተለይ በቀይ ሽብር ወቅት የጀርመን ሀገር የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የነበረው ዶክተር፣ ጀርመናዊት ሚስት የነበረዉ ዶክተር፣ ለሀገሬ ትንሽ ልስራ ብሎ፣ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ፣ወደ ሀገሩ ተመልሶ ይሠራ ነበር ብለን ዛሬ ብንመሰክር ይህንን የማይታመን አፈ ታሪክ አቁሙ ልንባል እንችላለን። ግን ሆኗልና መነገር አለበት። ካልተናገርንና ካልመሰከርን ደግሞ የታሪክ ተወቃሽ እንሆናለን። በእርግጥም እንመሰክራለን። ስለሆነም ቀደም ሲል የአዋሳ እርሻ ኮሌጅ ዲን የነበረውን የዶክተር ገረመው ኃይሌን ሥራ በጨረፍታም ቢሆን እንየው።
ዶክተር ገረመው ኃይሌ በአብዮቱ ወቅት የአዋሳ እርሻ ኮሌጅ ዲን ነበር። ረዥምና ቀጥ ያለ ቁመና የነበረው ሲሆን ዓይኖቹ ጎላ ጎላ ያሉ ነበሩ። ፊቱ ላይ ሽበት ጣል ጣል ያደረገበት ጥቅጥቅ ያለው ጢሙ የአንበሳ ግርማ ሞገስ ሰጥቶታል። በጣም የሚያስፈራው ግን ከዓይኖቹ ውስጥ የሚወጣው አስፈሪ አስተያየቱ ነበር። በሩቅ ሲመጣ ራሱን የማያምነው ተማሪ ሳይታይ ለማለፍ ጥረት ያደርጋል። ገና ኮሌጅ ሳይገቡ ተማሪዎች ስለ ዶክተር ገረመው ብዙ ብዙ በመስማት ፍርሃት ያድርባቸዋል። ቀድመው ኮሌጁ የገቡት ተማሪዎችም ስለ ዶክተሩ ጀግንነት ፣ ዲሲፕሊን እና ቆራጥነት እያጋነኑ አዲስ ለመጡት ተማሪዎች ማውራት የተለመደ ነው። ተማሪው ይኽንን እየሰማ ይርበደበዳል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ሀገሩን በጣም ይወዳል ተብሎም ይሞገስ ነበር።
ዶክተሩን ያወቅሁት ከቀይ ሽብር በኋላ አዋሳ እርሻ ኮሌጅ ገብቼ በነበረበት ወቅት ነው። ተማሪዎች በጣም ስለምንወደው አንተ ነበር የምንለው። ተማሪው አፍሮ ፀጉሩን አሳጥሮ፣ መጥፎ ፀባይ ያለው ፀባዩን አስተካክሎ እንዲመጣ ይነገረዋል። ጩኸት፣ መረበሽ ፣ መደባደብ የሚያስከፍለው ውድ የሆነውን የትምህርት እድል ማጣት መሆኑን ይገለጽለታል። ትምህርቱን ማጣት ደግሞ ለወታደርነት ተመልምሎ ወደ ጦርነት መሄድ ወይም ኑሮ የከበዳቸው ወላጆቻችን ላይ ሸክም መሆን ስለሆነ በጣም አስፈሪ ነበር። እሱን ባይሆን ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተዳድረውን የዶክተር ገረመውን ሥነ ሥርዓት መተዳደርን ማን ጠልቶት? ተማሪው የመጀመሪያ ጊዜ ከዶክተሩ ጋር የሚተዋወቅበት ስብሰባ (orientation) ይደረጋል። ዶክተሩ ተማሪውን በሞላ አንድ ጊዜ ይመለከትና ይጀምራል።
“አዋሳ ኮሌጅ ለእርሻ ከተመደበልን መሬት ጨምሮ 22 ሄክታር ነው። ። በዚህ ትንሽ ቦታ ከ2000 ሰው የሚበልጥ ሰው አስተዳደር ተብያለሁ። በዚህ ግቢ ውስጥ ሁላችንም በዘፈቀደ የምንኖር ከሆነ እርስ በርሳችን ተጋጭተን እናልቃለን። ስለዚህም መተዳደሪያ ሕግ ያስፈልገናል። የዚህ ግቢ ኃላፊ እኔ ነኝ ። ይህንን የምነግራችሁን ሕግ አስፈጽመዋለሁ። በዚህ አትጠራጠሩ። አብዮት ጥበቃም የሆንክ፣ ቀበሌ ተመራጭ የሆንክ እዚህ ግቢ ተማሪ ነህና ሸጉጥህንም ይሁን ጠብመንጃህን እዛው ደጅህ ጥለህ ና። እዚህ የመጣኸው ልትማር ነው። እዚህ ግቢ ከአንተ የሚያንስ ማንም የለም። ሌላው ቀርቶ እነዚህ ተስፈኛ የሚባሉት፤ እዚህ እየሰሩ ከተማ ውስጥ የሚማሩ፣ የምንረዳቸው ልጆች እንኳን የአንተ የበላይህ ናቸው። የታዘዝከውን መፈጸም አለብህ። መጣላት፣ መደባደብ፣ ሁሉም ከኮሌጅ ያስባርራሉ። መዳራትም እንደዚሁ። ልትማሪ/ልትማር እንጂ ልትራቢ/ልትራባ አይደለም እዚህ የመጣሽው/የመጣኸው።”
በስብሰባዉ አዳራሽ ዉስጥ የነበርን ተማሪዎች ስንስቅ፣
“እውነቴን ነው የምለው ምን ትገለፍጣለህ? ድሮ ደርግ እረኛውን ነበር የሚልከው አሁንስ በጉን መላክ ጀመረ እንዴ? ልትማር ነው የመጣኸው ። ምግብ፣ አልጋ ፣ ለብቻህ ነው የሰጠንህ። ምንም የሚያዳርስህ የለም። ጠጅህን ተግተህ ስክሬ እመጣለሁ ብለህ እንዳታስብ ፣ ትጣላኛለህ። በጠፍ ጨረቃ ሰው አየኝ አላየኝ ብለህ ዕቃህን ጠቅልለህ ትወጣታለህ። ይህ ብቻ አይደለም ሳታጠና ብትቀርም እንደዚሁ ነው። ሻንጣህን እንኳን ለመሰብስብ ታፍርና ሰው ሳያይህ ነው የምትጠፋው፣ ስለዚህ ብታጠና ይሻላሃል። እኛ እናንተን ልናስተምር ተዘጋጅተን ነው የምንጠብቃችሁ። ትንሽ የእርሻ እውቀት አግኝታችሁ ይህንን መከረኛ ሕዝብ ትረዱታላችሁ ተብላችሁ ነው እዚህ የመጣችሁት ። እዚህ በድጋፍ ወረቀት፣ በማስፈራራት አልፋለሁ ብለህ ቀበሌ የተማርከውን ማስፈራራት ይዘህ ከመጣህ አይሆንም ። የበረታው ነው የሚመረቀው ፣ የደከመው ዕቃውን ጠቅልሎ ይሄዳል።”
ተማሪው ጸጥ እረጭ ብሎ ነው የሚያዳምጠው። ትንሽ ዝም ብሎ ወደ ተማሪዎቹ እየተመለከተ ቆይቶ አንዱን ተማሪ፦
“አንተ እዚያ ጋ ደረትህን ገልብጠህ የተቀመጥከው አብዮት ጥበቃ ነበርክ?”
ማንን ማየቱ እንደሆነ ስላልገባን እርሱ በሚመለከትበት አካባቢ ያለን ተማሪዎች እርስ በርሳችን መተያየት ጀመርን።
“አንተ እዛ ጋ ደረትህን ገልብጠህ የተቀመጥከው።”
አንዱ ተነስቶ “እኔን ነው?” ብሎ ጠየቀ።
“አዎ አንተም ብትሆን።” ተማሪው “አልነበርኩም” ብሎ መለሰ ።
“ጥሩ አንተ ካልሆንክ፣ እዚህ ውስጥ ቀበሌ ያዙኝ ልቀቁኝ የምትል አብዮት ጥበቃ ወይም የወጣቶች ሊቀመንበር የነበራችሁ አትጠፋም። እሱን እዛው ጥለኸው ና እዚህ ግቢ የወገብ ሳይሆን የእውቀት ትጥቅ ነው የሚያስፈልግህ።” የሚነገረንን ሁለ ሰምተን በጸጥታ እንወጣለን።
በደርግ ዘመን ምንም እንኳን የሃገሪቱ ሁኔታ አሳዛኝ ደረጃ ላይ የነበረ ቢሆንም ሃገራቸው ውስጥ ተቀምጠው፣ “ከደርጉ አብዮት” እራሳቸውን አርቀው፣ የቻሉትን ለመሥራት ጥረት ያደርጉ የነበሩ ጀግኖች ዜጎች ነበሩ። በዚያን ዘመን ምሁራን ለሃገራቸው የሚችሉትን ለማበርከት ምን ያህል ፈታኝ ችግር ይገጥማቸው እንደነበር በቃላት ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው። ደርግ ምሁራንን ያስር፣ ይገርፍ፣ ይገድል እንደነበር መካድ አይቻልም። ያ ጀግና ዲን ግን በተራ ካድሬዎች እየተዋከበ፣ በማያምነው ሥርዓት ውስጥ ተቀምጦ ለሃገሪቱ ልማትና እድገት ይበጃል የሚላቸውን የግብርና ባለሙያዎች ሲያሰለጥን ነበር። እረፍት ሳይኖረው ከአዋሳ ሳይወጣ ሙሉ ጊዜውን በግቢው ውስጥ በማሳለፍ የእርሻ ባለሙያዎች በወጉ እንዲማሩ ትልቅ ጥረት ያደርግ ነበር። ወቅቱ ለአንድ ካድሬ የማሰር፣ የመግረፍ፣ የመግደል መብት የተሰጠበት ስለነበር ዶክተሩ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በውጥረት ውስጥ ነበር የሚኖረው። ያም ሆኖ ግን ሃገር እናስተዳድራለን ከሚሉ ማሀይም ካድሬዎች ጋር በቆራጥነት እየተዋጋ፣ የተማሪውን መብት እያስጠበቀ፣ ሥነ ሥርዓት አስከብሮ ለዓመታት ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ የግብርና ባለሙያዎችን አስመርቋል። ዛሬ በሃገሪቱ ውስጥ በብዙ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ መለስተኛና ፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች የዚህ ጀግና ምሁር ውጤቶች ናቸው።
ዶክተር ገረመው በጣም የሚታወቀው አብዮቱን አለመደገፉ ነበር። ሃገሩን ይወዳል ግን ካድሬ፣ ፖለቲካ፣ ስብሰባ፣ የሚባል ነገር ያንገሸግሸዋል። ኮሌጁ ለትምህርት ብቻ እንዲውል ይታገላል። ይህ አቋሙ በክፍለሀገሩ ፖለቲከኞችም በጣም የሚታወቅ ነበር። በምዕራብ ጀርመን የተማረን ዶክተር የቀበሌ ተራ ፖለቲከኛ ጭቅጭቅ ምንም ባይገባው ለማንም አይደነቅም ወይም ኮሌጅ ለትምህርት የመጣው ተማሪ የሚናገረውን የማያውቅ የካድሬ ጭቅጭቅ ጆሮውን እንዳያደነቁረው ቢታገል አያስገርምም። ዶክተሩ ጎበዝ ተማሪ ማምረት እንጂ ራሱ እንደሚለው የቀበሌ ስንዴ የሚያከፋፍል ካድሬን ማምረትን አይሻም ነበር።
እውነት እንደሆነ ማረጋገጥ ባይቻልም አንድ የክፍለ ሃገሩ ካድሬ የመማሪያውን አዳራሽ ለቅዳሜና እሁድ ለስብሰባ ዶክተር ገረመውን ፍቃድ ይጠይቃል። ዶክተሩ እንደተለመደው አዳራሹ መማሪያ እንጂ መሰብሰቢያ አይደለም ብሎ ይከለክላል። ጮላው ካድሬ “ከተማራችሁት ይኸ አይጠበቅም ይለዋል።” መልስ የማያጣው ዶክተር ገረመው “ማትሪክ እንደ ከዘራ ጠሞብህ ነው እንጂ ኮሌጁን አልዘጋነውም፣ ደፍሮ ገብቶ ተምሮ ዲን መሆን ነው” አለው ይባላል።
ይህንን ዓይነት ሁኔታ በተለይ ሥራ ከገባን በኋላ ምን ያህል የልማት ነፍሰ ገዳይ መሆኑን በተግባር ያየነው ነው። ለእርሻ የተመደበ ትራክተርን አስገድደው ወስደው የቤት ዕቃ የሚያመላልሱ የኢሠፓ አባላት ብዙ ነበሩ። ለግብርና የተመደበውን መኪና ወስደው ገበሬው ጋ መሄዴ የሚገባው ሠራተኛ እንዲቀር የተገደደበት ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ። ለእርሻ የሚያገለግሉ ዶዞሮች ለእግር ኳስ ሜዳ ያስተካክሉ ተብለው በአውራጃ ኢሠፓ (በዘመኑ አነጋገር አመራር ተሰጥቶበት )ተወስደው የእርሻው ጊዜ ያለፈበትም ወቅት ነበር። እምቢ ማለት ደግሞ የሚያስከትለውን መገመት ይቻላል። የኢሠፓ አባላትን ያስቀየመ ምን እንደሚደርስበት የኢሠፓአኮ ምሥረታ አዋጅ በአጭሩ የኢሠፓ አባላትን ያስቀየመ ወይም ለማስቀየም ያሰበም እንኳን ወንጀለኛ ነው የሚል ሕግ ደንግጎ ነበር።
ዶክተሩ ስለተማሪው ምግብ መኝታ ቁጥጥር ያደርጋል። አንድ ቀን እራት ሰዓት ላይ ዶክተሩ ተማሪዎች ምግብ መመገቢያ አዳራሽ ይመጣል። አንድ ተማሪ ኮፍያ ሳያወልቅ ሲበላ ያየዋል። ተማሪውን ዶክተሩ አጠገቡ ቆሞ ይመለከተው ጀመር። ተማሪው ደነገጠ። ግን ዶክተሩ ለምን እንደሚመለከተው አላወቀም። ተማሪው ሊነሳ ሲል ዶክተሩ ቁጭ በል አለው። መፋጠጥ ሆነ። በመጨረሻም ዶክተሩ ኮፍያ አድርገህ ነው የምትበላው? ብሎ ጠየቀው። እስከ አሁን አስታውሰዋለሁ ልጁ ኮፍያውን አንስቶ መሬት ላይ በድንጋጤ ወረወረው። ዶክተሩም ስቆ ጥልት ሄደ። ከዚያም ሴቶቹ ጋ ሄዶ ከሚበሉት ምግብ አጉርሱኝ አለ። ምግቡ አልጣፈጠውም መሰለኝ የምግብ ቤት ኃላፊውን አቶ አሰፋ የሚባለውን አስጠራው። አሰፋ መጥቶ አጠገቡ ቆመ። ዶክተሩ የዛሬው እራት ቀይ ነው ወይስ አልጫ ? ብሎ ጠየቀው። አሰፋ በምሳ ሰዓት ምግብ ስለተረፈ ቀይኑ እና አልጫውን . . . ብሎ ሊያስረዳ ሲጀምር አቋረጠውና ዶክተሩ ቀይ ነው ወይስ አልጫ ? ብሎ ደግሞ ጠየቀው። አሰፋ ደንግጦ የሚናገረው ጠፋው። ዶክተሩ ከዛሬ ጀምሮ ቀይና አልጫ እንዳታደባልቅ ብሎ ከለከለው። ከዚያ በኋላ ለተማሪውም የተደባለቀ ወጥ መቅረብ አቆመ።
እራሴ የነበርኩበትና የተከታተሉኩትን ምንም ጊዜ የማልረሳው አንድ ጉዳይ አለ ። ከክፍለ ሃገሩ ጽሕፈት ቤት የተላከ አንድ ካድሬ የወጣት ማህበር ለማቋቋም ወደ ኮሌጁ ይመጣል። ሁላችንም እንሰባሰባለን ። ካድሬው የነቃና የተደራጀ ምሁር ለአብዮቱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳናል። ከዚያም የወጣቶች ማህበር ማቋቋም አስፈላጊ ስለሆነ እንድናቋቁም ያሳስበናል። ችግሩ የዶክተሩንና የብዙሃኑን መምህራን አቋም ስለምናውቅ ማን ይመረጥ? አብዮቱ በጣም በማይደገፍበት የኮሌጅ ግቢ ማነው የወጣት ማህበር የሚመረጠው? ማነው ሊቀመንበር ሆኖ የሚመረጠውስ? ማነውስ የሚጠቁመውስ? ሂደቱ ብዙ ጊዜ ወሰደ። ካድሬውም ተናደደ። ምሳ ሰዓት አለፈ። ከምሳ በኋላ ምርጫ እናደርጋለን አለና ምሳ ተበላ። ከምሳ በኋላም ጸጥታ ሰፈነ። ተማሪውም አልመርጥም አለ። ከብዙ ዝምታ በኋላ ዶክተሩ ተጠራ።
በዚያ በሚያስፈራ ድምጹ “ለምንድነው የተፈለግሁት?” ብሎ ጠየቀ። “ተማሪዎቹ አንመርጥም ብለዋል” ካድሬው መለሰ ። “ካልመረጡ ታዲያ ምን ላድርግ?” ዶክተሩ ካድሬውን ጠየቀው። ካድሬው በንዴት “የኢትዮጵያ አብዮት እንኳን አዋሳ እርሻ ኮሌጅ ሱማሌ ገብቷል። እዚህ ግቢ የተጠቀጠቁትን ፀረ አብዮተኞችን ማጽዳት አያቅተንም”። ሲል አምርሮ ተናገረ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ዶክተሩ ዓይን ላይ ሊደርስ የሚችለው ችግር ታየ ። ከዚያም በሚያሳዝን ድምጽ ፡ –
“ባለፉት ዓመታት ብዙ ችግር ሁላችንም አይተናል። ይህ እዚህ የምታዩት ሰውዬ ደግሞ የሚዝተው ያየነውን ሁሉ አሰቃቂ ተግባር እዚህ ለመድገም ነው። እኔ በበኩሌ ይህንን ዳግም ለመመልከት አልፈልግም። ምን አለ የምትችሉ ከሆናችሁ መርጣችሁ ብንገላገል። ለማንኛውም ኃላፊነቱን ለአንተ(ለካድሬው) ሰጥቻለሁ” ብሎት ጥሎት ሄደ ።
ተማሪዎችም ይህ ችግር ከእሱም በላይ እንደ ሆነ ተረዳን። በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠቁመን መርጠን ጨረስንና ከዚያ አስቃቂ አደጋ ተገላገልን። ነገር ግን የተመረጠው ኮሚቴ ምንም የረባ ጉዳይ ሳይፈጽም ተመረቅን ። አዎ “የደርጉ አብዮት” በግድያ አዋሳ እርሻ ኮሌጅ ቀርቶ ብዙ ቦታ መድረስ ችሏል። ይህ ሂደት ብዘዎቹን ሃገራቸውን የሚወዱ አስተማሪዎችን ከሃገር አባርሯል ወይም ገሏል።
ዶክተር ገረመው በዚህ ስቃይ ውስጥ ኖሮ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ የእርሻ ባለሙያዎችን ለሃገሪቷ ስላፈራ ሊመሰገን ይገባዋል።ከእርሱ ጎን የቆሙ አስተማሪዎችም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። በየቦታው ብዙ ያልተነገረላቸው የውጭ ሃገር የተንደላቀቀ ኑሮን ትተው ለሃገራቸው ብዙ የሠሩ ምንም ሳይነገርላቸው ታሪካቸው ተቀብሮ ቀርቷል። ምንአልባትም ዛሬ ያንን የቀውጢ ቀን ሸሽቶ የበረረ ፣ ለሃገሩ ምንም አስተዋፅዖ ያላበረከት እንደ ጀግና ሲመሰገን ለሃገሩ የሞተ ሊወቀስ ይችላል። ለማጠቃለል ያህል ከሁሉ በላይ የማስታውስው የመጨረሻ በምረቃችን ቀን ዶክተሩ የተናገረውን በማስታወስ ነው። ብዙ ይናገራል ተብሎ ሲጠበቅ፡-
“እዚህ ኮሌጅ ሁለት ዓመት ቆይታችኋል። ትንሽ በጣም ትንሽ ዕውቀት ገብይታችኋል። ታዲያ ይህቺን ዕውቅት ይዘህ ገበሬውን ከመርዳት ተቆጥበህ ገበሬውን አዛዥህ ነኝ ካልከው፣ አትረባም ማለት ነው። ገበሬው ከአንተ በላይ ብዙ ያውቃል። ከገበሬው እየተማርክ ስለ እርሻ ካስተማርከው ደግሞ ትንሽ ለሃገርህም፣ ለገበሬውም ትንሽ ጥቅም ትሰጣለህ ። አይ ብለህ ግን ካድሬ ልሁን ካልክ እዚህ እኛም ጋር መምጣት አያስፈልግህም ነበር። ጨርሻለሁ።” ብዙ ይናገራል የተባለው ዶክተር በሁለት ደቂቃ ጨረሰ።
ብዙዎቻችን ወደ ሥራ ስንሰማራ የዶክተር ገረመው የአደራ ቃል ጭንቅላታችን ውስጥ ያቃጭል ነበር። በተለይ በደርግ አገዛዝ ጊዜ በነበረው ድርቅ ወቅት በሠፈራና ስግሰጋ ውስጥ እንሰራ የነበርነው የእርሻ ባለሙያዎች ችግሩን ተጋፍጠናል። የሰው ሕይወት እየረገፈ ባለበት ወቅት የኢሠፓ አባላት አመራር ምን ያህል ችግር ይፈጥሩ እንደነበር ገና ያልተጻፈ ጉድ ነው። ሰው መኖር በማይችልበት አካባቢ መስፈር አለባቸው ተብሎ የተወሰዱ የሰሜን ሰዎች በበሽታ ሲያልቁ አይተናል። እንደ ዶክተር ጠንካራ ያልሆኑ ዶክተሮች የተሳሳተውን የኢሠፓ አመራር ሲያደንቁም ተሰምተዋል። የሚያሳዝን ብዙ ታሪክ ተፈጽሟል።
ዶክተር ገረመውን እየፈራነው ወደድነው፣ እየወደድነው አከበርነው፣ እያከበርነው ቃሉን ለመፈጸም ሞከርን፣ የተሳካልንም ያልተሳካልንም ነበርን። ሌሎች ብዙ ስለ ዶክተር ገረመው ብዙ ያልተነገሩ ስላሉ ወደ ፊት ሌሎች ጸሐፊዎች በተለይ የእርሻ ሳይንስን በሚመለከት በሰፊው ይጽፋሉ የሚል እምነት አለኝ።